Skip to content
Home » የአእምሮ መታወክ » ራስን ማጥፋትን መከላከል

ራስን ማጥፋትን መከላከል

እርስዎ ወይም እርስዎ የሚያውቁት ሰው እንዲህ አይነት ቀውስ ውስጥ ከሆነ

ወደ 988፣ ራስን ማጥፋት እና ተያያይዝ ጉዳዮች ጣቢያ በመደወል ወይም የጽሑፍ መልእክት በመላክ ይነጋገሩ። ይህ ጣብያ ራስን ማጥፋት እና ተያያዥ ችግሮች ውስጥ ላለ፣ እንዲሁም በድባቴ ለተጠቃ ማንኛውም ሰው ሚስጥሩ የተጠበቀ የ24-ሰዓት የስልክ መስመር እርዳታ ይሰጣል። ለሕይወት አስጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆኑ ወይም የሆነ ሰው ሲያገኙ ወደ 911 ይደውሉ። የማህበራዊ ሚዲያ ጓደኛዎ የሚለጥፋቸው ነገሮች እንግዳ እና ደህንነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ከሆነ ለሚዲያው አጋዥ ቡድኖችን ሪፖርት ያድርጉ። እነርሱ ለግለሰቡ የሚያስፈልገውን ርዳታ ለማድረግ በራሳቸው መንገድ ይንቀሳቀሳሉ።

ራስን ማጥፋት እና ቀውስ የሕይወት መስመር 988 አዶ

ራስን ማጥፋት ምንድን ነው?

ራስን ማጥፋት አሳሳቢ የሆነ የህዝብ ጤና(public health) ጉዳይ ሆኗል። እ.ኤ.አ. በ 2020 ራስን ማጥፋት በጠቅላላ ዩናይትድ ስቴትስ 12 ኛው የሞት መንስኤ ሲሆን ከ 45,900 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ራስን ማጥፋት ውስብስብ እና አሳዛኝ ነው፤ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ መከላከል ይቻላል። አንድ ሰው ራሱን ሊያጠፋ እንደሆነ ስለሚጠቁሙ ምልክቶች እና እንዴት እርዳታ ማግኘት እንደሚቻል ማወቅ ህይወትን ለማዳን ይረዳል።

ራስን ማጥፋት ሰዎች ሕይወታቸውን ለማጥፋት በማሰብ ራሳቸውን ሲጎዱ እና በዚህም ምክንያት ሲሞቱ ነው።

ራስን የማጥፋት ሙከራ ደግሞ ሰዎች ህይወታቸውን ለማጥፋት በማሰብ ራሳቸውን ሲጎዱ ነገር ግን ሳይሞቱ ሱቀሩ ነው።

ስለ ራስን የማጥፋት ሙከራዎች እና ራስን ስለማጥፋት ስናወራ “የተሳካ ራሳን ማጥፋት” ወይም “የከሸፈ ራስን የማጥፋት ሙከራ” እና የመሳሰሉ ቃላትን ከመጠቀም ልንቆጠብ ይገባል፤ ምክንያቱም እነዚህ ንግግሮች ብዙ ጊዜ አሉታዊ ትርጉም አላቸው።

ራስን ማጥፋትን በተመለከተ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ራሳቸውን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎች የሚከተሉ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ይታዩባቸዋል፦

  • መሞት እንደሚፈልጉ ያወራሉ ወይም ራስን ማጥፋት ይፈልጋሉ
  • ባዶነት እንደሚሰማቸው ወይም ተስፋ እንደቆረጡ ወይም ለመኖር ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ያወራሉ
  • እስር ውስጥ እንዳሉ እንደሚሰማቸው እና ለችግራቸውም ምንም መፍትሄ እንደሌለው ያወራሉ
  • ሊቋቋሙት የማይችሉት ስሜታዊ ወይም አካላዊ ህመም ይሰማቸዋል
  • ለሌሎች ሸክም ስለመሆን ያወራሉ
  • ከቤተሰብ እና ከጓደኞች መራቅ ያበዛሉ
  • ጠቃሚ ንብረቶችን ለሌሎች እንዲሁ ይሰጣሉ
  • ከጓደኞች እና ከቤተሰብ ጋር ይሰናበታሉ
  • ነገሮችን በስርዓት ያደራጃሉ፤ ኑዛዜ ይጽፋሉ።
  • ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ ከባባድ አደጋዎችን ይዳፈራሉ፤ ለምሳሌ በፍጥነት ማሽከርከር
  • ስለ ሞት ብዙ ጊዜ ያወራሉ ወይም ያስባሉ

ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት አደጋ ላይ እንዳሉ የሚያሳዩ ሌሎች ወሳኝ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • ከፍተኛ የስሜት መለዋወጥ ማሳየት፤ ለምሳሌ በድንገት ከከፍተኛ ሀዘን ወደ ከፍተኛ መረጋጋት ወይም ደስተኛነት መለወጥ።
  • ራሳቸውን ስሚያጠፉበት መንገድ እቅድ ያዘጋጃሉ ወይም ራስን ስለ ማጥፋት ዘዴዎች ኢንተርኔት ላይ ያስሳሉ። ክኒኖች ማከማቸት ወይም ሽጉጥ መግዛት ሌሎች ምልክቶች ናቸው።
  • ከባድ የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ሀፍረት እንደሚሰማቸው ያወራሉ።
  • አልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ያበዛሉ።
  • መጨነቅ እና መበሳጨት ያበዛሉ።
  • የተለመደውን የምግብ ወይም የመኝታ ኡደታቸውን ይቀይራሉ።
  • መቆጣት እና ስለበቀል ማወራትም ሌላኛው ምልክት ነው።

ራስን ማጥፋት ለጭንቀት ስሜት የሚሰጠ ጤናኛ ምላሽ አይደለም። ራስን የማጥፋት ሀሳቦች ወይም ድርጊቶች የከፍተኛ ጭንቀት ምልክት ስለሆኑ ችላ ሊባሉ አይገባም።

  1. ራስን የማጥፋት ምልክት የሚታይበትን ሰው “ራስህን ለማጥፋት እያሰብክ ነው?” ብለህ ጠይቀው። ጥያቄው ቀላል አይደለም፣ ነገር ግን ጥናቶች እንደሚያሳዩት ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ራሳቸውን ሊያጠፉ እንደሆነ መጠየቅ ራሳቸውን እንዲያጠፉ አይገፋፋም፤ ወይም ራስን የማጥፋት ሀሳባቸው እንዲጨምር አያደርግም።
  2. ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን አድርግ፡ ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ገዳይ ከሆኑ ነገሮች እና ቦታዎች ማራቅ ራስን ማጥፋትን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም፣ ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያለን ሰው ራስን የማጥፋት እቅድ እንዳለው መጠየቅ እና ገዳይ ከሆኑ ነገሮች ማራቅ ትልቅ ለውጥ ሊፈጥር ይችላል።
  3. ሁሌም አጠገባቸው ሁን: ንግግራቸውን በጥሞና አድምጥ፤ እንዲሁም ምን እንደሚያስብ እና ምን እንደሚሰማው ለማወቅ ሞክር። ምርምሮች ራስን ስለ ማጥፋት ማውራት እና እውቅና መስጠት ራስን የማጥፋት እድልን ከመጨመር ይልቅ እንደሚቀንሱ ይጠቁማሉ።
  4. ከእርዳታ ማዕከላት ጋር እንዲገናኙ እርዷቸው: 988 ራስን የማጥፋት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጣብያ ስልክ ቁጥር ነው፤ ይህንን ቁጥር በስልክዎ ይመዝግቡ። እንዲሁም ከቤተሰብ አባል፣ ጓደኛ፣ መንፈሳዊ አማካሪ፣ ከአእምሮ ጤና ባለሙያ እና መሰል ታማኝ ሰው ጋር በማገናኘት ማገዝ ይችላሉ።
  5. ግንኙነትዎን አያቋርጡ: ችግሩ በመጠኑ ከተቀረፈ በኋላ ወይም ከእንክብካቤ ማዕከላት ከወጡ በኋላም ግንኙነት አለማቋረጥ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ላሉ ሰዎች ክትትል ማድረግ ራስን የማጥፋት እድልን ይቀንሳል።

ራስን የማጥፋት እድልን ከፍ እና ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድናቸው?

በየትኛውም ፆታ፣ እድሜ እና ጎሳ ያሉ ሰዎች ራስን ለማጥፋት አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ። ራስን ከማጥፋት ጋር በተያያዘ ያሉ ባህርያት ውስብስብ ናቸው፤ እናም ራስን ማጥፋት አንድ ምክንያት የለውም። ራስን የማጥፋት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው

  • ድባቴ፣ ሌሎች የአእምሮ መታወኮች እና አደንዛዥ እጽ።
  • የመዳን ተስፋቸው ዝቅተኛ የሆኑ በሽታዎች
  • በፊት የተደረጉ ራስን የማጥፋት ሙከራዎች
  • የአእምሮ ሕመም ያለበት ወይም አደኝዛዥ ዕፅ የሚጠቀም ቤተሰብ ወይም ዘመድ መኖር።
  • ራሱን ያጠፋ ቤተሰብ ወይም ዘመድ መኖር
  • በቤተሰብ ውስጥ ለአካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት መጋለጥ
  • በቤት ውስጥ ሽጉጥ ወይም ሌላ የጦር መሳሪያ መኖር
  • በቅርቡ ከእስር ቤት መፈታት

ራስን የማጥፋት ሐሳብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተመሳሳይ ሀሳብ ውስጥ ካሉ ጓደኞች፣ የቤተሰብ አባላት ወይም ታዋቂ ሰዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ከፈጠሩ ራሳቸውን የማጥፋት እድላቸው ከፍ ሊል ይችላል።

ራስን የማጥፋት እድልን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ  ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት አይሞክሩም፤ እናም ከነዚህ ሰዎች የትኛው ከሀሳብ አልፎ ወደ ተግባር እንደሚሸጋገር መለየት አስቸጋሪ ነው።

ምንም እንኳን ራስን የማጥፋት እድልን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከፍ ያለ ራስን የማጥፋት አደጋ ውስጥ ያለው ራስን የማጥፋት የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን እያሳየ ያለ ሰው ነውና አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልገዋል።

አስጨናቂ የሕይወት ክስተቶች (የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፣ ከሕግ ወይም ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች) እና በማህበራዊ ህይወት የሚፈጠሩ ችግሮች (ውርደት፣ ትንኮሳ፣ ጉልበተኝነት፣ መድልዎ እና ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነቶች የሚፈጠሩ ችግሮች) ራስን የማጥፋት እድልን ሊያባብሱ ይችላሉ፤ በተለይ ደግሞ ራስን የማጥፋት እድልን ከፍ ከሚናደርጉ ሁኔታዎች ጋር አብረው ሲከሰቱ።

ብዙ ጊዜ ቤተሰብ እና ጓደኞች ግለሰቡ ራስን የማጥፋትን የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሲታይበት ያውቃሉ፤ እናም የሚወዱት ሰው የአእምሮ ጤና ህክምና እንዲያገኝ በመርዳት የመጀመሪያውን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ይሄንን እንዴት ማድረግ እንዳለብዎ እርግጠኛ ካልሆኑ፣ የአእምሮ ሕመሞችን ለመርዳት የተዘጋጀውን የNIMHን ገጽ ይጎብኙ።

ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን መለየት

ሁለንተናዊ ፍተሻ፦ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ሶስቱ-ጥያቄዎች የተሰኘው የምርመራ ዘዴ የድንገተኛ ክፍል ባለሙያዎች ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ጎልማሶችን ለይተው እንዲያውቁ ይረዳል። በሆነ ጊዜ ተመራማሪዎች በየትኛውም ምክንያት ወደ ድንገተኛ ህክምና ክፍል የመጡ ታካሚዎችን በሙሉ መርምረው፣ ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ታካሚዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል። ተመራማሪዎቹ ራስን የማጥፋት አደጋ ውስጥ ያለ ሰውን የመፈተሻ መሳርያን በመጠቀም ራሳቸውን የሚያጠፋ ጎልማሳዎች ቁጥር በየዓመቱ በሦስት ሚሊዮን እንደሚጨምር ገምተዋል።

ኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ መዛግብትን በመጠቀም ራስን የማጥፋት አደጋን መተንበይ፦ የNIMH ተመራማሪዎች ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር በአሜሪካ የርበኞች ጉዳይ ዲፓርትመንት የጤና እንክብካቤ በሚደረግላቸው የቀድሞ ወታደሮች መኻል ምን ያህል ራስን የማጥፋት አደጋ እንዳለ ለመተንበይ የሚረዱ የኮምፒውተር ሶፎትዌሮችን አዘጋጅተዋል። ሌሎች የጤና ጥበቃ ድርጅቶችም ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ለመለየት ከኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ መዛግብት የሚገኙ መረጃዎችን መጠቀም ጀምረዋል።

ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ላሉ ሰዎች ምን ምን ዓይነት ሕክምናዎች እና ቴራፒዎች ይሰጣሉ?

ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት ውጤታማ እና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ጣልቃገብነቶች ወሳኝ ናቸው።

አጭር ጣልቃገብነቶች

  • የደህንነት እቅድ፦ ለራስ የተበጀ የደህንነት እቅድ ራስን የማጥፋት ሃሳቦችን እና ድርጊቶችን እንደሚቀንስ መረጃዎች ያሳያሉ። ታካሚዎች ከሀኪማቸው ጋር በመመካከር ሽጉጥ፣ ክኒን፣ መርዝ እና መሰል ገዳይ መሳርያዎችን ከአካባቢያቸው የሚያስወግዱበትን እቅድ መንደፍ አለባቸው። በእቅዱ ታካሚዎች ራስን በማጥፋት ሀሳብ በሚሞሉበት ጊዜ ሊረዱ የሚችሉ የመቋቋሚያ ስልቶች መዘርዘር አለባቸው።
  • ስልክ በመደወል መከታተል፦ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለራስን የማጥፋት አደጋ የተጋለጡ ሰዎል አበረታች የስልክ ጥሪዎች ሲደርሳቸው ራሳቸውን የማጥፋት እድላቸው የሚቀንስ ሲሆን በጎ እና ሰላማዊ ባህሪ እንዲያመጡ እና እርዳታ እንዲፈልጉ ይበረታታሉ።

ሳይኮቴራፒ

ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ሰዎችን የሚረዱ በርካታ የቴራፒ አይነቶች አሉ (ከዚህ በታች ይመልከቱ)። እነዚህ ቴራፒዎች ግለሰቡን እንደገና ከመሞከር ሊያግዱ ይችላሉ።

  • Cognitive Behavioral Therapy ሰዎች አስጨናቂ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ የሚረዱ አዳዲስ መንገዶችን እንዲማሩ ይረዳቸዋል። CBT ሰዎች የአስተሳሰብ ዘይቤአቸውን እንዲያውቁ እና ራስን የማጥፋት ሀሳቦች በሚፈጠሩበት ጊዜ አማራጭ እርምጃዎችን እንዲያስቡ ይረዳል።

መድሃኒት

ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች መድኃኒ ሲታዘዝላቸው እና ሲጠቀሙ ይሻላቸዋል። ታካሚዎች ለነሱ የሚሰራውን ምርጡን መድሃኒት ወይም የመድሃኒት ጥምረት እና ትክክለኛውን ዶዝ ለማግኘት ከሀኪማቸው ጋር በቅርበት መስራት አለባቸው። ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ብዙ ጊዜ የአእምሮ ሕመም ወይም የአደንዛዥ ዕፅ ሱስ አለባቸው፤ እናም መድሐኒት እና ቴራፒ በጥምረት ሲጣቸው ጥሩ መሻሻል ያሳያሉ።

ክሎዛፒን በዋናነት ስኪዞፈሪንያ ያለባቸውን ሰዎች ለማከም የሚያገለግል አንቲሳይኮቲክ መድኃኒት ነው። እስካሁን ድረስ፣ ስኪዞፈሪንያ ወይም ስኪዞአፌክቲቭ ዲስኦርደር ባለባቸው በሽተኞች ላይ ተደጋጋሚ ራስን የማጥፋት አደጋን ለመቀነስ ከዩኤስ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (FDA) ፈቃድ ያለው ብቸኛው መድኃኒት ነው።

መድሀኒት ከታዘዘልዎ ስለሚከተሉ ነገሮች እርግጠኛ ይሁኑ፦

  • የሚወስዷቸው መድሃኒቶች ያሏቸው ስጋቶች እና ጥቅሞች ምን ምን እንደሆኑ መረዳትዎን ለማረጋገጥ ከሀኪምዎ ጋር ይወያዩ።
  • ከሀኪምዎ ጋር ሳይነጋገሩ መድሃኒት መውሰድ አያቁሙ። መድሃኒቱን በድንገት ማቆም የሕመም መጨመርን ሊያስከትል ይችላል፤ እንዲሁም ሌሎች ጥሩ ያልሆኑ ወይም አደገኛ የሆኑ መዘዞችም ሊኖሩ ይችላሉ።
  • የጎንዮሽ ጉዳቶችን በተመለከተ ማንኛውንም ስጋት ሲመለከቱ ወዲያውኑ ለሀኪምዎ ያሳውቁ። የዶዝ ለውጥ ወይም የተለየ መድሃኒት ያስፈልግዎት እንደሆነ ለመወሰን ሀኪምዎ ይረዱዎታል።
  • ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች ከኖሩ ለ FDA MedWatch Adverse Event Reporting Program ድረገጽ ወይም በዚህ ስልክ 1-800-332-1088 ሪፖርት ያድርጉ። እርስዎ ወይም ሀኪምዎ ሪፖርት መላክ ይችላሉ።

ስለ መድሃኒቶች የቅርብ ጊዜ መረጃ ለማግኘት፣ ሀኪምዎን ያነጋግሩ ወይም የFDA ድህረ ገጽን ይጎብኙ።

የትብብር እንክብካቤ

የትብብር እንክብካቤ በቡድን ላይ የተመሠረተ የአእምሮ ጤና እንክብካቤ አቀራረብ ነው። የስነምግባር ጤና አጠባበቅ አስተዳዳሪ ከሰውየው፣ ከዋናው ሀኪም እና ከአእምሮ ጤና ስፔሻሊስቶች ጋር በመተባበር የህክምና እቅድ ያዘጋጃል። የትብብር እንክብካቤ ድባቴን ለማከም እና ራስን የማጥፋት ሃሳቦችን ለመቀነስ ውጤታማ መንገድ እንደሆነ ታይቷል።

የአእምሮ ጤና ችግሮችን በተመለከተ እንዴት እርዳታ ማግኘት እችላለሁ?

እርዳታ የት ማግኘት እንደሚችሉ ካላወቁ፣ የጤና ባለሙያ ጋር ይሂዱ እና ህጋዊ ፈቃድ ወዳለው የአእምሮ ጤና ባለሙያ ይጠቁሙዎታል፤ ለምሳሌ ወደ ሳይካትሪስት ወይም ሳይኮሎጂስት ሊጠቁምዎ ይችላል። ወደ ህክምና ተቋም ከመሄድዎ በፊት ስለ ህክምና ተቋማት ቅድመ ግኝዛቤ የሚያስጨብጡ ምክሮችን ያግኙ

የአደንዛዥ እጽ እና የአእምሮ ጤና አገልግሎት አስተዳደር ድረገጽን በመጠቀም በአካባቢዎ ያሉ የአእምሮ ጤና አገልግሎት ማእከላትን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ።

ራስን ማጥፋትን በተመለከተ የተጻፉ የNIMH ምርምር ጽሑፎችን ከየት ማግኘት እችላለሁ?

NIMH በዩናይትድ ስቴትስ ራስን ማጥፋትን በመቀነስ ረገድ በጎ ተጽእኖ ሊኖራቸው የሚችል ተስፋ ሰጭ ምርምሮችን ይደግፋል። ምርምር ራስን የማጥፋት አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን የመለየት አቅማችንን ለማሻሻል እና ውጤታማ ህክምናዎችን ለማዘጋጀት በከፍተኛ ደረጃ እየረዳ ነው። የNIMH ተመራማሪዎች ራስን ማጥፋትን የመከላከል ፕሮግራሞችን በጤና ጣቢያ፣ በማህበረሰብ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፍትህ ስርአቶች እና ሌሎች መንገዶች እንዴት ውጤታማ በሆነ ሁኔታ መተግበር እንደሚቻል ጥናት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

የNIMH ምርምር ተቀዳሚ ትኩረቶች ምን እንደሆኑ እና ራስን ማጥፋትን መከላከልን በተመለከተ ስለ ወጡት የቅርብ ጊዜ ምርምሮች የበለጠ ይወቁ።

ራስን ማጥፋትን ስለ መከላከል የት ልማር እችላለሁ?

ነፃ ብሮሹሮች እና ሊጋሩ የሚችሉ ሀብቶች

የፌዴራል ግብአቶች

  • ጥቁር አሜሪካውያን ወጣቶች እና ራስን ማጥፋት፡ ይህ ሪፖርት በዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና የሰብአዊ አገልግሎት ዲፓርትመንት የተዘጋጀ ሲሆን፣ “Sound the Alarm: Black Suicide is a Crisis in America” በሚል ርዕስ ለተዘጋጀው የ2019 የጥቁር ካውከስ ጎንግረስ ሪፖርት የተሰጠ ምላሽ ነው። ሪፖርቱ የወጣቶች ራስን የማጥፋት መጠን በያንዳዱ ዘር እና ጎሳ ምን ያህል እንደሆነ፣ ወጣቶች ላይ ስለሚታዩ ራስን የማጥፋት ባህሪያት፣ ስለአደጋዎች እና የመከላከያ ሁኔታዎች፣ ስለ እርዳታ መንገዶች እና ስለ ቀሩ የእውቀት ክፍተቶችን ይመረምራል።
  • ራስን ማጥፋትን መከላከልን የተመለከተ የመረጃ ማዕከል (SPRC)፦ ብሔራዊ ራስን ማጥፋትን የመከላከል ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰራ በፌዴራል የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ብቸኛው የመርጃ ማዕከል (SPRC) ነው። SPRC በSAMHSA የሚደገፍ ነው።
  • የአሜሪካ ህንዳያን እና የአላስካ ተወላጆች(AI/AN): ብሔራዊ ራስን ማጥፋትን የመከላከል ስትራቴጂክ እቅድ፥ በጎሳዎች፣ በጎሳ ድርጅቶች፣ በከተማ የህንድ ድርጅቶች እና የህንድ ጤና አገልግሎቶች (IHS) ትብብር ራስን ማጥፋትን ለመከላከል የሚሰራ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው።
  • የIHS ራስን ማጥፋትን የመከላከል እና የእንክብካቤ ፕሮግራም ጣቢያ፦ ይህ ድርጅት ራስን ማጥፋትን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ እና ማህበረሰቦችን እና ግለሰቦችን ራስን ከማጥፋት ጋር በተያያዘ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚረዱ መርጃዎችን ያቀርባል።

This post is also available in: English (እንግሊዝኛ)

Index