Skip to content

ADHD ምንድን ነው?

ADHD ማለት ሰዎች ትኩረት ማድረግ እንዳይችሉ እና እንዳይረጋጉ የሚያደርግ የአእምሮ መዛባት ነው። ADHD ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉ ምልክቶች ይታይባቸዋል፦

  • 1: Inattention: ትኩረት ማድረግ ያለመቻል ችግር ሲሆን ምልክቱ የሚታይባቸው ሰዎች በስራቸው ላይ መቆየት፣ ትኩረታቸውን መቆጣጠር እና ተደራጅቶ መቀመጥ አይችሉም። ነገር ግን ያልቻሉት እምቢተኛ ስለሆኑ ወይም የግንዛቤ እጥረት ስላለባቸው አይደለም።
  • 2: Hyperactivity: መንቀዥቀዥ ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ሲሆን ምልክቱ የሚታይባቸው ሰዎች መረጋጋት የሚገባቸው ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳ ይንቀዠቀዣሉ ወይንም ከመጠን በላይ ያወራሉ። ብዙ ጊዜ አዋቂ ሰዎች ላይ ረፍት አልባ ወይም ተናጋሪ በማድረግ ይገለጣል።
  • 3: Impulsivity: ይህ ምልክት ያለባቸው ሰዎች ነገሮችን በሚገባ ሳያገናዝቡ ይከውናሉ ወይም ራሳቸውን መቆጣጠር አይችሉም። ላደረጉት ነገር ወዲያ ወጤቱን ማየት ይፈልጋሉ ወይም መታገስ አይችሉም። ሰዎችን በንግግር ከስራቸው ያቋርጣሉ፤ እንዲሁም ትልልቅ ውሳኔዎችን በሚገባ ሳገናዝቡ ይወስናሉ።

አንድ ሰው ADHD እንዳለበት የሚያሳዩ ምልክቶች ምንድ ናቸው?

አንዳንድ ADHD ያለባቸው ሰዎች በዋነኝነት የሚታይባቸው ምልክት ትኩረት ማድረግ አለመቻል ነው። ሌሎች ደሞ ከመጠን በላይ ንቁ መሆን እና አለመረጋጋት ያሳያሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እነዚህ ሁለቱም ምልክቶች ይታዩባቸዋል።

ማንኛውም ሰው መጠነኛ የማተኮር ችግር፣ መንቀዥቀዥ እና አለመረጋጋት ሊታይበት ይችላል። ነገር ግን ADHD ባለባቸው ሰዎች ላይ እነዚህ ነገሮች፦

  • – የበለጠ ከባድ ናቸው።
  • – ብዙ ጊዜ ይከሰታሉ
  • – በማህበራዊ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ከሰዎች ጋር ጥሩ መስተጋብር እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ

ትኩረት ማድረግ ያለመቻል ችግር

ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉ ምልክቶች ይታዩባቸዋል፦

  • – ወሳኝ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ባለማስተዋል በትምህርት ቤት፣ በሥራቸው ወይም በሌሎች ተግባራት ላይ ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ።
  • – በጨዋታዎች፣ በትምህርት ገበታ፣ በንግግሮች ወይም እንደ ንባብ ባሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ለማድረግ ይቸገራሉ
  • – ሰዎች በቀጥታ ሲያናግሯቸው የማያዳምጡ ይመስላሉ።
  • – መመርያዎችን በመከተል አንድን ስራ በቅደም ተከተል ማከናወን፣ ሀላፊነትን በሚገባ እና የጊዜ ገደቦችን በጠበቀ መልኩ መፈጸም ላይ ችግር አለባቸው
  • -መስራት ያለባቸውን ነገሮች ማደራጀት፣ ቁሳቁሶችን ስርዓት ማስያዝ እና በእቅድ መመራት ይከብዳቸዋል።
  • – ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ የአአምሮ ስራን የሚጠይቁ ተግባራትን (ለምሳሌ ለተማሪዎች የቤት ስራ መስራት፣ ለአዋቂዎች ደግሞ ሪፖርት ማዘጋጀት፣ ቅፆችን መሙላት እንዲሁም ረጅም ጽሑፎች ማንበብ) ለሌላ ጊዜ ማራዘም እና በጊዜው ማከናወን አለመቻል።
  • – እርሳስ፣ መጽሃፎች፣ መሳሪያዎች፣ የኪስ ቦርሳ፣ ቁልፎች፣ የወረቀት ስራዎች፣ መነፅር እና የሞባይል ስልኮችን የመሳሰሉ አስፈላጊ እቃዎች በየጊዜው ይጠፉባቸዋል።
  • – ከስራቸው ከሚሰሩት ነገር ጋር ባልተያያዙ ነገሮች በቀላሉ ይረበሻሉ
  • – የእለት ስራቸውን ማከናወን ይረሳሉ፣ ለምሳሌ የስልክ ጥሪ መመለስ እና ቀጠሮ ማክበር ወዘተ

መንቀዥቀዥ – ራስን አለመቆጣጠር

Hyperactivity impulsivity ያለባቸው ሰዎች የሚከተሉ ምልክቶች ያሳያሉ

  • – ተረጋግተው መቀመጥ ሲገባቸው ብዙ ይንቀሳቀሱ
  • – የመማርያ ክፍል ውስጥ፣ የሥራ ቦታ ወይም መሠል ቁጭ ማለት ሚገባቸው ቦታዎች ላይ መቀመጫቸውን ትተው ይሄዳሉ።
  • – መሮጥ ወይም መንጠልጠል ያበዛሉ፣ በትልልቅ ልጆች እና ጎልማሶች ላይ እረፍት ማጣት ይታይባቸዋል
  • – በጨዋታዎች ላይ መረጋጋት ይቸግራቸዋል
  • መቼም ዝም ብለው መቀመጥ አይችሉም ወይም ሁልጊዜም እንቅስቃሴ ላይ ናቸው።
  • – ከመጠን በላይ ያወራሉ
  • – ተጠይቀው ሳይጨርሱ ይመልሳሉ፣ ሌሎች ሲያወሩ ያቋርጣሉ ወይም ተራ ሳይጠብቁ ይናገራሉ። የሌሎችን አረፍተ ነገር ይጨርሳሉ
  • – በምንም ነገር ተራ መጠበቅ ይከብዳቸዋል
  • – በጨዋታ፣ በሰዎች ንግግርና ስራ ጣልቃ እየገቡ ሰው ያቋርጣሉ

የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ማዕከላት አንዳንድ ጊዜ ADHD ን ይመረምራሉ እናም ያክማሉ። እንዲሁም ለሰዎች ጠልቅ ያለ ምርመራ የሚያኙበትን የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን እና የስነ-አእምሮ ሐኪም ወይም ክሊኒካል ሳይኮሎጂስቶችን ይጠቁማሉ

አንድ ሰው የ ADHD ምርመራ ሊደረግለት ይገባል ብሎ ለመደምደም፣ ግለሰቡ ላይ የሚታዩ የትኩረት ማጣት እና/ወይም የመንቀዥቀዥ ምልክቶች ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ወይም ረጅም ጊዜ የቆዩ፣ የሰውዬውን የስራ ህይወት የሚረብሹ እና የግለሰቡን የተለመደ ባህርይ የመቀር ደረጃ የደረሱ መሆን አለባቸው። ውጥረት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ጭንቀት፣ ድብርት እና ሌሎች አካላዊ ህመሞች ከ ADHD ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስለዚህ የሕመሙን መንስኤ ለማወቅ ጥልቅ ምርመራ ያስፈልጋል።

አብዛኛዎቹ ADHD ያለባቸው ህጻናት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት አመታት ምርመራ ይደረግላቸዋል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወይም አዋቂ ሰው የ ADHD ምርመራ እንዲደረግለት ምልክቶቹ ከ12 ዓመት እድሜ በፊት መታየት አለባቸው።

የ ADHD ምልክቶች ከ3 እስከ 6 እድሜ ሊታዩ እና በጉርምስና እና በጉልምስናም እድሜም ሊቀጥሉ ይችላሉ። የ ADHD ምልክቶች ከስሜት ወይም ከዲሲፕሊን ችግሮች ጋር ተመሳስለው ሊሸውዱን ወይም ትኩረት የማድረግ ችግሮች ባላቸው ህጻናት ላይ ሙሉ ለሙሉ ላይታዩ ይችላሉ። ይህም የምርመራው መዘግየት ሊያስከትል ይችላል። ADHD ያለባቸው ነገር ግን ያልተመረመሩ አዋቂዎች በትምህርታቸው ደካማ የነበሩ፣ በሥራቸው ችግር ያለባቸው እና ከሰው ጋር ያላቸው ግንኙነትም ብልሹ ሊሆን ይችላል።

የ ADHD ምልክቶች ግለሰቡ በዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በጊዜ ሂደት ሊለወጡ ይችላሉ። ADHD ያለባቸው ትንንሽ ልጆች ላይ የሚታዩት ዋነኛ ምልክቶች መፍጠን እና መንቀዥቀዥ ናቸው። ልጁ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሲደርስ ትኩረት የማጣት ምልክት ይበልጥ ጎልቶ ሊወጣ እና ህፃኑ በትምህርቱ ወጤታማ እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል። በጉርምስና ወቅት፣ ከመጠን በላይ ችኩልነት እና መንቀዥቀዝ እየቀነሰ ይሄዳል። የመረበሽ ወይም ረፍት የመጣት ምልክትች መታየት ይጀምራሉ፣ ነገር ግን ትኩረት የማድረግ ችግር ሊቀጥል ይችላል። ADHD ያለባቸው ብዙ ታዳጊዎች ከግንኙነት ጋር የተያያዙ እና የማህበራዊ ህይወት ችግሮች ይታይባቸዋል። ትኩረት ማጣት እና እረፍት ማጣት እስከ አዋቂነት ድረስ ሊቀጥሉ ይችላሉ።

የ ADHD መዘዞች ምንድን ናቸው?

ተመራማሪዎች የ ADHD መንስኤ ምን እንደሆነ እርግጠኛ አይደሉም። ብዙ ጥናቶች ግን ዘረመል ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ያመለክታሉ። እንደሌሎች ብዙ በሽታዎች፣ ADHDም ምናልባት የብዙ ምክንያቶች ጥምረት ውጤት ነው። ተመራማሪዎች ከዘረመል በተጨማሪ በ ADHD የመያዝ እድልን ሊያሳድጉ የሚችሉ አካባቢያዊ፣ የአንጎል ጉዳት እና አመጋገብ የመሳሰሉ ምክንያቶችንም እያጠኑ ነው።

ADHD ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ የተለመደ ነው። ADHD ያለባቸው ሴቶች በዋነኛነት ትኩረት የማድረግ ችግር ይታይባቸዋል። ADHD ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ትምህርትን በአግባቡ መከታተል አለመቻል፣ ጭንቀት፣ የባህርይ ችግር፣ ድብርት እና አደንዛዥ እጽ መጠቀም እና መሰል ችግሮች ይታይባቸዋል።

ADHD እንዴት ይታከማል?

ለ ADHD መድሀኒት ባይኖርም አሁን ያሉት ህክምናዎች ምልክቶችን ይቀንሳሉ፤ እንዲሁም ተጠቂው ስራዎቹን በአግባቡ እንዲሰራ ይረዳሉ። ሕክምናውም መድሃኒት፣ የስነ-ልቦና ሕክምና፣ ትምህርት ወይም ስልጠና፣ ወይም የእነኚህን ቅልቅል ያካትታል።

መድሃኒት

ለብዙ ታማሚዎች የADHD መድሀኒቶች መንቀዥቀዥን እና ረፍት አልባነትን ይቀንሳሉ፤ እንዲሁም የማተኮር፣ የመስራት እና የመማር ችሎታቸውን ያሻሽላሉ። አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰው የሚሰራውን ትክክለኛውን መድሐኒት ከማግኘታችን በፊት ብዙ የተለያዩ መድሃኒቶችን ወይም ዶዞችን መሞከር ጠቃሚ ነው። መድሃኒቱን የሚወስድ ማንኛውም ሰው በሐኪም ትዕዛዝ እና ቅርብ ክትትል መውሰድ አለበት።

አነቃቂ መድሐኒቶች ADHDን ለማከም በጣም የተለመደው የመድኃኒት ዓይነት “አነቃቂ መድሐኒት” የሚባሉት ናቸው። ምንም እንኳን “አነቃቂ” ተብሎ በሚጠራ መድሐኒት ADHDን ማከም ያልተለመደ ቢመስልም፣ ዶፓሚን እና ኖሬፒንፊ’ን የመሳሰሉ በማሰብ አቅም እና በትኩረት ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ የአንጎል ኬሚካሎች በመጨመር ውጤታማ ለውጥ ያመጣል።

በህክምና ክትትል ስር ከሆነ አነቃቂ መድሃኒቶች ደህና እንደሆኑ ይቆጠራሉ። ነገር ግን፣ ልክ እንደሌሎች መድሃኒቶች፣ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖራቸው ይችላል፤ በተለይም አላግባብ ጥቅም ላይ ከዋሉ ወይም ከተወሰነው መጠን በላይ ከተወሰዱ። እናም ተማሚውን የሚከታተል የጤና ባለሙያ አቅራቢያው መኖር አለበት።

አነቃቂ ያልሆኑ መድሐኒቶች ሌሎች ጥቂት የ ADHD መድሃኒቶች አነቃቂ ያልሆኑ ናቸው። እነዚህ መድሃኒቶች ከአበረታች መድሃኒቶች በተለየ መስራት ለመጀመር ረጅም ጊዜ ይወስዳሉ። ነገር ግን የትኩረት ችግርን እና መረጋጋት ያለመቻልን ሊያሻሽሉ ይችላሉ። ዶክተሮች አበረታች ያልሆነ መድሃኒቶች የሚያዙት አበረታች መድሐኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች ሲኖራቸው፣ ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ ወይም ሁለቱ መድሐኒቶች ሲጣመሩ ውጤታማነታቸው የሚጨምር ከሆነ ነው።

ምንም እንኳን በU.S የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር (FDA) ADHDን ለማከም የተከለከለ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጸረ-ድባቴ መድሐኒቶች ለብቻቸው ወይም ከአበረታች መድሃኒት ጋር ተቀላቅለው ADHDን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላሉ። ፀረ-ድባቴ መድሃኒቶች ሁሉንም የ ADHD ምልክቶች ሊያክሙ ይችላሉ። እናም ለተጠቂው ግለሰብ አበረታች መድሃኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳቶች ካስከተሉ ይህ ጸረ-ድባቴ መድሐኒት ይታዘዝለታል። ግለሰቡ ከADHD በተጨማሪ የጭንቀት፣ የድብርት ወይም ሌላ የስሜት መቃወስ በሽታዎች ካሉበት ፀረ-ድባቴ መድሐኒት ከአበረታች መድሐኒት ጋር ተዳምሮ ቢሰጠው በጣም ውጤታማ ነው። አነቃቂ ያልሆኑ የ ADHD መድሃኒቶች እና ፀረ-ድባቴም የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖራቸው ይችላል።

ዶክተሮች እና ታካሚዎች አብረው ከሰሩ ምርጡን መድሃኒት፣ ዶዙን እና የተሻለውን የመድሃኒት ጥምረት ለማግኘት ይቀላቸዋል። ስለ መድሃኒቶች የቅርብ ጊዜ መረጃ ለማግኘት፣ ሀኪሞችን ማናገር ጥሩ አማራጭ ነው። እንዲሁም የኤፍዲኤ ድህረ ገጽን ይጎብኙ።

ሳይኮቴራፒ እና ማህበራዊ የስነ ልቦና ህክምና

ADHD ያለባቸው ግለሰቦች እና ቤተሰቦቻቸው ምልክቶቹን ለመቆጣጠር እና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአቸውን ለማሻሻል የሚረዱ ብዙ ልዩ ቴራፒዎች እና ማህበራዊ የስነልቦና ህክምና ዘዴዎች አሉ

እድሜያቸው ለትምህርት በደረሱ ልጆች የብስጭት፣ የንጭንጭ እና የቁጣ ባህርያት በሀኪም ከመታየታቸው በፊት እዚያው በቤተሰብ ውስጥ ሊዳብርባቸው ይችላል። አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ ወላጆች እና ልጆች ልዩ እርዳታ ሊፈልጉ ይችላሉ። የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ወላጆችን ስለ ADHD እና እንዴት ቤተሰብን እንደሚጎዳ ሊያስተምሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ህፃኑ እና ወላጆቹ አዲስ ክህሎቶችን፣ አመለካከቶችን እና እርስ በርስ የመተሳሰሪያ መንገዶችን እንዲያዳብሩ ይረዷቸዋል.

ADHD ላለባቸው ለህጻናት እና ታዳጊዎች የሚሰጡ ሁሉም ዓይነት ቴራፒዎች የወላጆች ንቁ ሚና እና ተሳትፎ የሚጠይቁ ናቸው። ከተጠቂው ልጅ ጋር (ያለ ወላጅ ተሳትፎ) ለብቻ የሚደረጉ የሳይኮቴራፒ ህክምናዎች የADHD ምልክቶችን ለመቆጣጠር እና ባህሪን ለማሻሻል ውጤታማ አይደሉም። ይህ ዓይነቱ ህክምና ከ ADHD ጋር አብሮ ሊከሰቱ የሚችሉ የጭንቀት እና የድባቴ በሽታዎችን ለማከም የበለጠ ውጤታማ ናቸው።

የባህርይ ቴራፒ አንድ ሰው ባህሪውን እንዲለውጥ ለመርዳት ያለመ የሳይኮ ቴራፔ ህክምና ነው። ይህ ህክምና የታካሚውን የትምህርት ቤት አሳይመንት ወይም ልሎች ስራዎችን ማገዝን አሊያም በአስቸጋሪ ስሜት ውስጥ ሲሆን አብሮ በመሆን ማገዝን ሊያካትት ይችላል። የባህሪ ህክምና ታካሚን የሚከተሉትን ያስተምራል፦

  • 1: እንዴት ስሜቱን መቆጣጠር እንዳለበት
  • 2: የተፈለገውን የባህርይ መሻሻል ሲያመጣ፣ ለምሳሌ ንዴቱን መቆጣጠር ሲችል ወይም ከመተግበሩ በፊት ማሰብን ሲለማመድ በራሱ እንዲኮራ

ቴራፒስቶች ህጻናትን ተራቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ አሻንጉሊቶችን ተጋርተው መጫወት እንዳለባቸው፣ በሚፈልጉበት ጊዜ እርዳታ እንዲጠይቁ፣ እንዴት ለተረብ መልስ መስጠት እንዳለባቸው እና የመሳሰሉ ማህበራዊ ክህሎቶችን ሊያስተምሩ ይችላሉ። ቴራፒስቶች ህጻናትን ተራቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ አሻንጉሊቶችን ተጋርተው መጫወት እንዳለባቸው፣ በሚፈልጉበት ጊዜ እርዳታ እንዲጠይቁ፣ እንዴት ለተረብ መልስ መስጠት እንዳለባቸው እና የመሳሰሉ ማህበራዊ ክህሎቶችን ሊያስተምሩ ይችላሉ። የሰዎችን የፊት ገጽታ እና አነጋገር የማንበብ እና ተገቢ መልስ የመስጠት ችሎታም የማህራዊ ክህሎት ስልጠናው ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ።

ኮግኒቲቭ የባህርይ ህክምና ደግሞ አንድ ሰው ሀሳቦቹን እና ስሜቶቹን እንዲያውቅ እና እንዲቀበል እንዲሁም የትኩረት እና የመረጋጋት ችግሮችን ማሻሻል እንደሚችል ያግዛል። በተመጫሪም ቴራፒስቱ ታካሚው ከህክምናው ጋር ተያይዞ የሚመጡበትን የኑሮ ለውጦች እንዲያስተካክል ያበረታታዋል፤ ለምሳሌ አንድ ነገር ከማድረጉ በፊት ማሰብ እንዳለበት ወይም አላስፈላጊ ሪስኮችን የመውሰድ የውስጥ ግፊቶቹን እንዲቋቋም እና የመሳሰሉ።

የቤተሰብ እና የጋብቻ ቴራፒ ደግሞ ቀሪው የቤተሰብ አባል ADHD ያለበት አባል ወይም የትዳር አጋር የሚያሳያቸውን የሚረብሹ ባህሪያት የሚቆጣጠርበትን፣ ተጠቂው እንዲሻሻል የሚረዳበትን እና ከተጠቂው ጋር የሚኖረው ግንኙነት የሚሻሻልበትን ዘዴ የሚጠቁም የቴራፒ አይነት ነው።

የወላጅነት ክህሎት ስልጠና ደግሞ ወላጆች በልጆቻቸው አወንታዊ ባህሪያትን ሲመለከቱ እንዲያበረታቱ እና እንዲሸልሙ ያስተምራል። ወላጆች ልጆች የተፈለጉ ባህርያትን ሲያሳዩ አወንታዊ አስተያየት እንዲሰጡ እና እዚያው በቦታው ላይ እንዲያበረታቷቸው፣ ያልተፈለጉ ባህርያትን ስያሳዩ ደግሞ ችላ እንዲሉ ወይም በመመከር የልጆችን ባህርይ የሚያሻሽሉበትን ዘዴ ያስተምራል።

ልዩ የትምህርት ገበታ ባህርይ የማሻሻያ ቴራፒ ደግሞ ህጻናት እና ታዳጊዎች በትምህርት ገበታቸው የADHD ምልክቶችን እንዲቆጣጠሩ እና ከእኩዮቻው ጋር ያላቸውን ተግባቦት በማሻሻል ረገድ ውጤታማ የሆነ ቴራፒ ነው። ይህ ቴራፒ የባህርይ ማሻሻያ ዕቅዶችን፣ የተደራጀ ሰው የመሆኛ ዘዴዎችን እና የትምህርት ክህሎት የማሻሻያ መንገዶችን ማስተማርን ሊያካትት ይችላሉ። ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ዘና ብለው መቀመጥ እንዲችሉ መፍቀድ፣ የክፍል ስራ ጫናዎችን መቀነስ፣ እና ረዘም ያለ ጊዜን ፈተና በመስራት እንዲያሳልፉ ማድረግ ከሚወሰዱት እርምጃዎች ሊያካትቱ ይችላሉ። እንዲሁም ትምህርት ቤቱ 504 እቅድ ተብሎ በሚጠራው አሰራር አማካኝነት የልዩ ትምህርት አገልግሎት እንደሚገባቸው ለተረጋገጠ ተማሪዎች “IEP” ተብሎ የሚጠራውን በግል የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይችላል።

ስለ አካል ጉዳተኞች ትምህርት ህግ (IDEA) የበለጠ ለማወቅ የዩኤስ የትምህርት መምሪያ የ IDEA ድህረ ገጽን ይጎብኙ።

ጭንቀት የመቆጣጠሪያ ዘዴዎችን ማወቅ ADHD ያለባቸው ልጆች ወላጆችን በብዙ ይጠቅማል፤ ለሚፈጠርባቸውን ጭንቀት ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡ እና ልጆቻቸውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲያስተናግዱ ይረዳቸዋል።

የድጋፍ ቡድኖች ውስጥ መሳተፍ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች እርስበርስ እንዲገናኙ እና ልምድ እንዲለዋወጡ ይረዳቸዋል። እነኚህ ቡድኖች የገጠማቸውን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች ለመወያየት፣ ስለተሻለ ስፔሻሊስት ሀኪሞች እና የህክምና ዘዴዎች መረጃ ለመለዋወጥ እና ከባለሙያዎች ጋር ለመነጋገር በመደበኛነት ይገናኛሉ።

በበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማእከል (ሲዲሲ) የሚደገፈው፣ ብሔራዊ የADHD መረጃ ማዕከል የተሰኘው፣ የADHD ተጠቂ ህጻናት እና አዋቂዎች(CHADDR) ፕሮግራም በዚህ ረገድ ብዙ መረጃዎች አሉት። ይህንን ማእከል በመስመር ላይ ማግኘት ይችላሉ። ወይም በስልክ ቁጥር 1-866-200-8098።

ስለ ሳይኮቴራፒ የበለጠ ይረዱ።

ADHD ያለባቸው ህጻናት እና አዋቂዎችን የሚረዱ ምክሮች

ለልጆች:

ወላጆች እና አስተማሪዎች ADHD ያለባቸው ህጻናት እንዲደራጁ እና መመሪያዎችን እንዲከተሉ የሚከተሉ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላሉ፦

  • የለተተለት ልማድን እና እቅድን በጥንቃቄ ተፈጻሚ ማድረግ። በየለቱ ከጠዋት እስከ መኝታ ሰአት ድረስ ተመሳሳይ የውሉ እቅድን መከተል በእቅዱ ውስጥ የቤት ስራ መስርያ ሰዓት፣ ቤት ውስጥ የመጫወቻ ሰዓት እና ከቤት ውጪ የመጫወቻ ሰዓቶች መካተት አለባቸው። ይህንን የውሉ እቅድ በፍሪጅ ላይ ወይም በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ይለጥፉ በእቅዱ ላይ ለውጦች ሲኖሩ በተቻለ መጠን አስቀድመው ይፃፉ።
  • የዕለት ተዕለት ዕቃዎችን ማደራጀት. ለሁሉም ነገሮች ቦታ ይኑርዎት። ( ለምሳሌ ልብስ፣ ቦርሳዎች እና መጫወቻዎች) እናም ሁሉንም ነገር በቦታቸው ያስቀምጡ።
  • የቤት ስራ እና ማስታወሻ ደብተር አዘጋጆችን በመጠቀም። ለትምህርት ቤት ቁሳቁስ እና አቅርቦቶች አዘጋጆችን ይጠቀሙ። ለልጅዎ ስራዎችን መጻፍ እና አስፈላጊ መጽሃፎችን ወደ ቤት ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ያሳውቁ.
  • ግልጽ እና ወጥነት ያለው መሆን ADHD ያለባቸው ልጆች ሊረዷቸው እና ሊከተሏቸው የሚችሏቸው ወጥ ህጎች ያስፈልጋቸዋል።
  • ደንቦች ሲከበሩ ውዳሴ ወይም ሽልማቶችን መስጠት። ADHD ያለባቸው ልጆች ብዙ ጊዜ ይገሰጻሉ፤ እንዲሁም እንደሚገሰጹ ይጠብቃሉ። የልጅዎትን ጥሩ ባህሪ መርመረው በሱም ያወድሱት።

ለአዋቂዎች፡-

አንድ ባለሙያ አማካሪ ወይም ቴራፒስት ADHD ያለበት አንድ አዋቂ ሰው ህይወቱን እንዴት ማደራጀት እንዳለበት በሚከተሉት ዘዴዎች ሊያስተምር ይችላል፦

  • የተለመዱ የእለት ተለት ተግባራትን ባለማዛነፍ ተፈጻሚ ማድረግ
  • የምንሰራቸውን የተለያዩ ተግባራት እና ስራዎች በቅድመ ተከተል መጻፍ
  • መርሐግብሮችን ለማቀድ የቀን መቁጠሪያ ካላንደር መጠቀም።
  • እንዳንረሳ የሚያደርጉ የማስታወሻ ደብተሮችን መጠቀም።
  • ቁልፍ፣ ደረሰኝ እና የወረቀት ስራዎች የሚቀመጡበት ልዩ ቦታ ማዘጋጀት
  • ትልልቅ ስራዎችን ለማስተዳደር በሚመች መልኩ አሳንሶ በክፍል ክፍል በማደራጀት ደረጃ በደረጃ ተፈጻሚ በማድረግ የስኬት እርካታን መጨመር።

ስለ ADHD የበለጠ የት ልማር እችላለሁ?

ነፃ ብሮሹሮች እና ሊጋሩ የሚችሉ መረጃዎች

መልቲሚዲያ

This post is also available in: English (እንግሊዝኛ)

Index