ሕክምናዎች
ቴራፒ (ሳይኮቴራፒ ወይም የንግግር ሕክምና ተብሎም ይጠራል) ስሜታዊና አእምሯዊ የጤና ችግሮችን ከሠለጠነ ባለሙያ ጋር በመነጋገር የሚፈቱበት የሕክምና መንገድ ነው። የተለያዩ የቴራፒ ዓይነቶች አሉ፤ እያንዳንዱም በተለየ መንገድ ይሠራል። ይህ ገጽ ከጤና ባለሙያ ጋር ለመወያየት እንዲረዳዎ ዋና ዋናዎቹን ዓይነቶች በአጭሩ ያስተዋውቃል።
ለሁሉም ሰው የሚሠራ አንድ ዓይነት ሕክምና የለም። ሰዎች ወደ ቴራፒ የሚመጡት በተለያዩ ምክንያቶች ነው፦ ካሳለፉት አሳማሚ ተሞክሮ ለማገገም፣ ውስጣዊ መረጋጋት ለማግኘት ወይም የዕለት ተዕለት ኑሮን በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም። ስለ አማራጮቹ ጊዜ ወስደው ይወቁ። ዓላማው ለእርስዎ ፍላጎት የሚስማማውን የቴራፒ ዓይነት እና ባለሙያ ማግኘት ነው።
ዋና ዋናዎቹ የቴራፒ ዓይነቶች፦
- የአስተሳሰብና የባህርይ ሕክምና (Cognitive-Behavioral Therapy – CBT)፦ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ሕክምና ነው። የማይጠቅሙ የአስተሳሰብ ልማዶችን ለይተው እንዲያውቁ እና ይበልጥ ጠቃሚ በሆኑ አስተሳሰቦች እንዲተኳቸው ያስተምራል። እነዚህን ልማዶች መለወጥ ስሜታዊ ጭንቀትን ለማቃለል ይረዳል።
- ሳይኮአናሊቲክ ቴራፒ (Psychoanalytic Therapy)፦ ያለፉ ተሞክሮዎች እና ሙሉ በሙሉ ያላስተዋሏቸው ስሜቶች በአሁኑ ሕይወትዎ ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ይመረምራል። እነዚህን መረዳት ወደፊት ለውጥ ለማምጣት ይረዳዎታል።
- ሂዩማኒስቲክ ቴራፒ (Humanistic Therapy)፦ እርስዎን እንደ ሙሉ ሰው በመመልከት በራስዎ ጥንካሬዎች ላይ ያተኩራል። ባለሙያው ያለ ፍርድ በመቀበል እና በመደገፍ ለራስዎ ያለዎትን ግምት እንዲያሳድጉ እና እንዲያድጉ ያግዛል። የጌስታልት ቴራፒ እና ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ ቴራፒ የዚህ ዓይነት ምሳሌዎች ናቸው።
- በአስተውሎት (ማይንድፉልነስ) ላይ የተመሠረቱ ሕክምናዎች (Mindfulness-Based Therapies)፦ ትኩረትዎን በአሁኑ ቅጽበት ላይ እንዲያደርጉ እና ሐሳቦችዎንና ስሜቶችዎን ሳይፈርዱባቸው እንዲቀበሉ ያስተምራሉ። ብዙ ጊዜ የአተነፋፈስ እና የሜዲቴሽን ልምምዶችን ይጠቀማሉ። እነዚህ ክህሎቶች በአስጨናቂ ጊዜ ለመረጋጋት ይረዳሉ።
- የቤተሰብ ሕክምና (Family Therapy)፦ የቤተሰብ አባላት አብረው ከባለሙያ ጋር ይገናኛሉ። ቤተሰቡ በርኅራኄ መነጋገርን፣ አለመግባባቶችን በመረዳዳት መፍታትን እና እርስ በርስ መደጋገፍን ይማራል።
ሌሎች የቴራፒ ዓይነቶችም አሉ፤ ለምሳሌ የሥነ ጥበብ ቴራፒ፣ የሙዚቃ ቴራፒ እና የጨዋታ ቴራፒ። እነዚህ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጹና እንዲረዱ ለማገዝ የፈጠራ ሥራዎችን ይጠቀማሉ። የትኛው ዓይነት ለእርስዎ እንደሚስማማ ለመወሰን የጤና ባለሙያ ሊረዳዎ ይችላል።
ከየት እንደሚጀምሩ እርግጠኛ ካልሆኑ የቤተሰብ ሐኪምዎን ይጠይቁ፤ ወይም ቴራፒስት እንዴት እንደሚያገኙ ያንብቡ።
እባክዎን ያስተውሉ፦ ይህ ድህረ-ገጽ ገና በመዘጋጀት ላይ ነው፤ ትርጉሞችም ሁልጊዜ ፍጹም ላይሆኑ ይችላሉ። ለምርመራ እና ለሕክምና ሁልጊዜ የባለሙያ ምክር ይጠይቁ።