ስለሚወዱት ሰው ሲጨነቁ
የሚቀርብዎት ሰው እንደ ወትሮው እንዳልሆነ አስተውለዋል። ነገሩ ከባድ መሆን አለመሆኑን እርግጠኛ አይደሉም፤ ሰውየውን ማሳፈርም ሆነ ሁኔታውን ማባባስ አይፈልጉም። ይህ መመሪያ ለእንዲህ ያለ ጊዜ የተዘጋጀ ነው።
አንድ ሰው እየተቸገረ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች
አንድ መጥፎ ሳምንት ማሳለፍ የሕይወት አካል ነው። ለውጦቹ ሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ሲቆዩ ወይም እየባሱ ሲሄዱ ግን ትኩረት ይስጡ፦
- ከወትሮው በጣም የበዛ ወይም በጣም ያነሰ እንቅልፍ መተኛት
- ከወትሮው በጣም ያነሰ ወይም በጣም የበዛ መመገብ፤ ክብደት መቀነስ
- ከቤተሰብ፣ ከጓደኞች፣ ከቤተ ክርስቲያን ወይም ከመስጊድ፣ አልያም ከማህበራዊ ስብሰባዎች መራቅ
- ቀድሞ ያስደስቱት በነበሩ ነገሮች ፍላጎት ማጣት
- ከወትሮው በተለየ መነጫነጭ፣ መረጋጋት አለመቻል ወይም በቀላሉ መቆጣት
- በሥራ ወይም በትምህርት መቸገር፣ ወይም መሠረታዊ የሆኑ ራስን የመንከባከብ ተግባራትን መተው
- መጠጥ ማብዛት፣ ወይም ጫት ወይም ሌሎች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አብዝቶ መጠቀም
- ‹‹ሸክም ሆንኩባችሁ›› ወይም ‹‹ምንም ነገር አይለወጥም›› የመሳሰሉ ነገሮችን መናገር
በማህበረሰባችን ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዴት ይገለጣል?
ብዙ ሰዎች ‹‹ድባቴ ይዞኛል›› አይሉም። ይልቁንም ስለ ሰውነታቸው ወይም ስለ ሐሳብ ይናገራሉ፦
- ራስ ምታት፣ የሆድ ሕመም፣ ደረትን ጭምቅ አድርጎ የሚይዝ ስሜት፣ ወይም በምርመራ ምክንያቱ ያልተገኘለት ሕመም
- የማያቋርጥ ድካም — ‹‹ሰውነቴ ደክሟል››
- ከልክ በላይ ማሰብ — ‹‹ሐሳብ በዛብኝ››፣ ‹‹ጭንቀት ያዘኝ››
- በጭንቅላት ወይም በልብ ላይ የሚሰማ የክብደት ወይም የማቃጠል ስሜት
እነዚህ የሕመም ስሜቶች እውነተኛ ናቸው። የስሜት ሥቃይ የሚገለጥባቸው መንገዶችም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ስለዚህ በቁም ነገር ይመልከቷቸው፤ ሰውየው ሐኪም ዘንድ እንዲሄድም ያበረታቱት።
ውይይቱን መጀመር
ጊዜውን ይምረጡ። ሌላ ሰው በሌለበት፣ ሳይቸኩሉ ይነጋገሩ፦ ቡና እየጠጡ፣ በእግር እየተጓዙ ወይም መኪና ውስጥ ሆነው። በእንግዶች ወይም በሌሎች ዘመዶች ፊት ጉዳዩን በፍጹም አያንሡ።
የደረሱበትን ድምዳሜ ሳይሆን ያዩትን ይናገሩ።
‹‹ሰሞኑን ብዙም አትተኛም፤ አስቤህ ነው። እንዴት ነህ?››
"You have not been sleeping much lately, and I have been thinking about you. How are you?"
‹‹ልፈርድብሽ አይደለም፤ ላዳምጥሽ ነው የምፈልገው።››
"I am not here to judge you. I just want to listen."
ከዚያ ያዳምጡ። ችግሩን መፍታት አይጠበቅብዎትም። ዝምታም ችግር የለውም። ‹‹ይህ በጣም ከባድ ነው›› ማለት ብቻ ይበቃል።
አንድ ተግባራዊ እርምጃ ይጠቁሙ።
‹‹አብረን ሐኪም ጋር እንሂድ? ቀጠሮውን እኔ ልያዝልህ።››
"Shall we go to the doctor together? I can make the appointment for you."
መራቅ ያለብዎት ነገሮች
- ‹‹አብዝተህ ጸልይ›› ወይም ‹‹በርታ›› ማለት። እምነት እውነተኛ የብርታት ምንጭ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ መልኩ ሲነገር ግን ሥቃዩ የራሱ ጥፋት እንደሆነ ለሰውየው ይነግረዋል።
- ‹‹ምን ጎደለሽ? ሁሉ ነገር አለሽ›› ማለት። ድባቴ ምስጋና ቢስነት አይደለም።
- ‹‹ለማንም አትንገር›› ማለት። ነገሩን መደበቅ እፍረትን ያባብሳል።
- ከሌሎች ጋር ማወዳደር፦ ‹‹ካንቺ የባሰ የተሠቃዩ ሰዎች አሉ።››
እምቢ ካለ
በመጀመሪያው ጊዜ እምቢ ማለት የተለመደ ነው። አይከራከሩ። ያቀረቡለት ሐሳብ በፈለገ ጊዜ እንደሚጠብቀው ይንገሩት፤ ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላም ጉዳዩን መልሰው ያንሡ። እስከዚያው ከጎኑ ይሁኑ፦ አብረው ይመገቡ፤ መጋበዝዎንም አያቋርጡ። የአእምሮ ጤና ባለሙያ ማየት ባይፈልግ እንኳ፣ የቤተሰብ ሐኪም ዘንድ ለመደበኛ የጤና ምርመራ ለመሄድ ሊስማማ ይችላል፤ ይህም ጥሩ ጅምር ነው።
አሁኑኑ የሚያሰጋ አደጋ ከሌለ በስተቀር አዋቂ ሰውን አስገድዶ ማሳከም አይቻልም።
ሕክምና ላይ ያለን ሰው መደገፍ
- በተግባራዊ ነገሮች ያግዙ፦ በመኪና ማድረስ፣ በቀጠሮ ሰዓት ልጆችን መጠበቅ፣ ቀጠሮዎችን ማስታወስ።
- መድኃኒቱን በታዘዘለት መሠረት መውሰዱን እንዲቀጥል ያበረታቱት። ሰዎች ብዙ ጊዜ መሻል ሲጀምሩ መድኃኒታቸውን ያቆማሉ፤ በዚህም ምልክቶቹ ሊመለሱ ይችላሉ። ማንኛውም ለውጥ መድኃኒቱን ካዘዘው ባለሙያ ጋር በመስማማት ሊደረግ ይገባል።
- ከመቆጣጠር ይልቅ ‹‹ምን ላግዝ?›› ብለው ይጠይቁ።
- ሚስጥሩን ይጠብቁ። እሱ ራሱ ካልፈቀደ በስተቀር፣ የነገርዎትን ነገር ለሰፊው ቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ ማህበሩ ወይም ለቤተ እምነቱ ምእመናን አያጋሩ።
- ጥሩ ሳምንታትም መጥፎ ሳምንታትም እንደሚኖሩ ይጠብቁ። ማገገም ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ ያለበት ጉዞ ነው።
ራስዎንም ይንከባከቡ
ሰውን መደገፍ ያደክማል። የራስዎን እንቅልፍ፣ ምግብ እና ጓደኝነት አይተዉ። እርስዎም ከሚያምኑት ሰው ወይም ከባለሙያ ድጋፍ መጠየቅዎ ራስ ወዳድነት አይደለም።
ሁኔታው አስቸኳይ ሲሆን
ከሚከተሉት አንዱን ካስተዋሉ አሁኑኑ እርምጃ ይውሰዱ፦ ሰውየው መሞት እንደሚፈልግ ወይም ሸክም እንደሆነ ሲናገር፣ ሕይወቱን የሚያጠፋበትን መንገድ ሲፈልግ፣ ንብረቱን ለሰዎች ሲሰጥ ወይም ሲሰናበት፣ ወይም ራሱን ወይም ሌሎችን እንዲጎዳ የሚያዝዙ ድምፆች ሲሰማ።
- በቀጥታ ይጠይቁ፦ ‹‹ሕይወትህን ለማጥፋት እያሰብክ ነው?›› መጠየቅዎ ሐሳቡን አያስጀምርበትም።
- ብቻውን አይተዉት፤ መድኃኒቶችን፣ የጦር መሣሪያዎችንና ሌሎች አደገኛ ነገሮችን ከሚደርስበት ቦታ ያርቁ።
- ለእርዳታ ይደውሉ። በአሜሪካ ወይም በካናዳ የሚገኙ ከሆነ ወደ 988 ይደውሉ ወይም የጽሑፍ መልእክት ይላኩ፤ አሁኑኑ የሚያሰጋ አደጋ ካለ ወደ 911 ይደውሉ። በሌላ አገር ከሆኑ በዓለም ዙሪያ ያሉ የአስቸኳይ እርዳታ መስመሮችን ይመልከቱ።