መዝገበ ቃላት · Glossary
በአእምሮ ጤና ዙሪያ በብዛት የሚነገሩ 48 ቃላት ቀለል ባለ አማርኛና በእንግሊዝኛ ተብራርተዋል። ለሐኪም ቀጠሮ ለመዘጋጀት፣ ሐኪም የነገረዎትን ለቤተሰብ ለማስረዳት ወይም አስተርጓሚ የተጠቀመውን ቃል ለማረጋገጥ ይጠቀሙበት።
ስለ አማርኛ ቃላቱ። ለብዙ የሕክምና ቃላት በአማርኛ አንድ ወጥ ስምምነት ያለው አጠራር ገና የለም፤ የተለያዩ ቃላት ጎን ለጎን ይነገራሉ። ከአንድ በላይ አጠራር የተለመደ ሲሆን ‹‹ሌሎች አጠራሮች›› በሚለው ሥር ተዘርዝረዋል። እርስዎ በሌላ ቃል የሚጠሩት ካለ ይጻፉልን።
ስሜቶችና ገጠመኞች · Feelings and experiences
- ውጥረት Stress ሌሎች አጠራሮች፦ ጫና
-
ሰውነታችንና አእምሯችን ለጫና የሚሰጡት ምላሽ ነው፤ ለምሳሌ የገንዘብ ጭንቀት፣ የሥራ ወይም የቤተሰብ ኃላፊነት ሲበዛ። ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ውጥረት የተለመደ ነው፤ ሳያቋርጥ ሲቀጥል ግን እንቅልፍን፣ ስሜትንና አካላዊ ጤናን ይጎዳል።
The body and mind's response to pressure or demands, such as money worries, work, or family responsibilities. Short-term stress is normal; stress that does not let up can harm sleep, mood, and physical health.
- ጭንቀት Anxiety ሌሎች አጠራሮች፦ የጭንቀት መታወክ · Anxiety disorder
-
ወደፊት ሊሆን ስለሚችል ነገር የሚሰማ ስጋት፣ ፍርሃት ወይም አለመረጋጋት ነው። ማንኛውም ሰው አልፎ አልፎ ይጨነቃል። ጭንቀቱ ከባድ ሆኖ ለወራት ሲቆይና የዕለት ተዕለት ኑሮን ሲያውክ ግን የጭንቀት መታወክ ሊሆን ይችላል፤ ይህም በሕክምና ይሻሻላል።
Worry, fear, or unease about what might happen. Everyone feels anxious sometimes. When the worry is strong, lasts for months, and gets in the way of daily life, it may be an anxiety disorder, which is treatable.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የድንጋጤ ጥቃት Panic attack ሌሎች አጠራሮች፦ ፓኒክ አታክ
-
በድንገት የሚመጣ ከባድ ፍርሃት ሲሆን የልብ ምት መፍጠን፣ የትንፋሽ ማጠር፣ መንቀጥቀጥ ወይም ማዞር የመሳሰሉ አካላዊ ምልክቶች አብረውት ይታያሉ። ብዙ ጊዜ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ጫፍ ደርሶ ይቀንሳል። በጣም ቢያስፈራም በራሱ አደገኛ አይደለም፤ የደረት ሕመም ካለ ግን ሐኪም ማየት ያስፈልጋል።
A sudden wave of intense fear with strong physical signs such as a racing heart, shortness of breath, shaking, or dizziness. It usually peaks within minutes. It feels frightening but is not dangerous in itself; chest pain should still be checked by a doctor.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ድባቴ Depression ሌሎች አጠራሮች፦ የመንፈስ ጭንቀት፣ ድብርት
-
የሕክምና ክትትል የሚያስፈልገው ሕመም እንጂ ድክመት ወይም የእምነት ማነስ አይደለም። ለሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ አብዛኛውን ቀን ማዘን፣ ባዶነት መሰማት ወይም ቀድሞ ያስደስቱ በነበሩ ነገሮች ፍላጎት ማጣትን ያስከትላል፤ ብዙ ጊዜም የእንቅልፍ፣ የምግብ ፍላጎት፣ የጉልበትና የትኩረት ለውጥ አብሮት ይታያል። በብዙ ሰዎች ላይ የሚከሰትና የሚታከም ሕመም ነው።
A medical condition, not a weakness or a lack of faith. It causes a low or empty mood, or loss of interest in things once enjoyed, most of the day for two weeks or more, often with changes in sleep, appetite, energy, and concentration. It is common and treatable.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ሐዘን Grief
-
የሚወዱትን ሰው ወይም ትልቅ ዋጋ ያለውን ነገር ሲያጡ የሚሰማ ተፈጥሯዊ ስሜት ነው። ሐዘን ሕመም አይደለም፤ የተወሰነ የጊዜ ገደብም የለውም። ከብዙ ወራት በኋላም ሥቃዩ ሳይቀንስ የዕለት ተዕለት ኑሮን መምራት ካቃተ ግን ከባለሙያ ጋር መነጋገር ይረዳል።
The natural response to losing someone or something important. Grief is not an illness and has no fixed timetable. If, after many months, the pain stays so strong that daily life is not possible, talking with a professional can help.
- የሥነ ልቦና ጉዳት Trauma ሌሎች አጠራሮች፦ ትራውማ፣ አሰቃቂ ገጠመኝ
-
እንደ ጥቃት፣ ጦርነት፣ አደገኛ ጉዞ፣ አደጋ ወይም በደል ያለ አስፈሪና እጅግ የሚያሳዝን ገጠመኝ በአእምሮ ላይ ትቶት የሚሄደው ዘላቂ ጉዳት ነው። ቅዠት የሞላበት ሕልም፣ በትንሽ ነገር መደንገጥ ወይም ገጠመኙን የሚያስታውሱ ነገሮችን መሸሽ የተለመዱ ምላሾች ናቸው፤ በሕክምናም ይሻሻላሉ።
The lasting emotional effect of a frightening or deeply distressing event, such as violence, war, a dangerous journey, an accident, or abuse. Reactions like nightmares, jumpiness, or avoiding reminders are common and can be treated.
ተጨማሪ ያንብቡ → - መታከት Burnout ሌሎች አጠራሮች፦ በርንአውት፣ ከፍተኛ የሥራ ድካም
-
ለረጅም ጊዜ በቆየ ጫና ምክንያት የሚመጣ ጥልቅ የአካልና የስሜት ድካም ነው፤ ብዙ ጊዜ ከሥራ ብዛት፣ ቤተሰብን ከመንከባከብ ወይም ብዙ ሥራ በአንድ ላይ ከመሥራት ይመነጫል። በዕረፍት የማይለቅ ድካም፣ ለነገሮች ግድ ማጣትና የሥራ ብቃት መቀነስ ምልክቶቹ ናቸው። ራሱን የቻለ የሕመም ስም ባይሆንም ወደ ድባቴ ወይም ጭንቀት ሊያመራ ይችላል።
Deep physical and emotional exhaustion from long-lasting pressure, often from work, caregiving, or holding several jobs. It shows up as tiredness that rest does not fix, feeling detached, and doing less well than usual. It is not a diagnosis, but it can lead to depression or anxiety.
- ማኒያ Mania ሌሎች አጠራሮች፦ ከልክ ያለፈ የስሜት መነቃቃት
-
ለቀናት ወይም ከዚያ በላይ የሚቆይ ከተለመደው በጣም የላቀ ደስታ፣ ቁጡነትና ጉልበት የሚታይበት ጊዜ ነው፤ በጣም ጥቂት እንቅልፍ መበቃት፣ በፍጥነት መናገር፣ የሐሳብ መሯሯጥና ገንዘብ ያለልክ ማውጣትን የመሰሉ አደገኛ ውሳኔዎች ይታያሉ። የባይፖላር ዲስኦርደር ዋና መገለጫ ነው።
A period of unusually high or irritable mood and energy lasting days or longer: needing very little sleep, talking fast, racing thoughts, and risky decisions such as overspending. It is a key feature of bipolar disorder.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ሳይኮሲስ Psychosis ሌሎች አጠራሮች፦ ከእውነታ ጋር ያለ ግንኙነት መዛባት
-
አንድ ሰው እውነተኛውንና እውነት ያልሆነውን ለመለየት የሚቸገርበት ሁኔታ ነው። ሌሎች የማይሰሙትን ሊሰማ ወይም የማያዩትን ሊያይ፣ አልያም እውነት ያልሆነ ነገርን አጥብቆ ሊያምን ይችላል። ሳይኮሲስ የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሩት የሚችል የሕመም ምልክት ነው፤ ቀደም ብሎ መታከም ይረዳል።
A state in which a person has trouble telling what is real from what is not. They may hear or see things others do not, or hold fixed beliefs that are not true. Psychosis is a medical symptom with several possible causes; early treatment helps.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የሌለን ነገር መስማት ወይም ማየት Hallucination ሌሎች አጠራሮች፦ ሃሉሲኔሽን፣ ቅዠት
-
በእውን የሌለን ነገር መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት ወይም በሰውነት ላይ መሰማት ነው፤ ለምሳሌ ማንም ሳይናገር ድምፅ መስማት። ለሚሰማው ሰው ግን ፍጹም እውነት ሆኖ ይሰማዋል።
Hearing, seeing, smelling, or feeling something that is not actually there, such as hearing voices when no one is speaking. To the person it feels completely real.
- የተሳሳተ ጽኑ እምነት Delusion ሌሎች አጠራሮች፦ ዲሉዥን
-
እውነት ያልሆነና ግልጽ ማስረጃ ቢቀርብም የማይለወጥ ጽኑ እምነት ነው፤ ለምሳሌ ‹‹ሰዎች ይከታተሉኛል›› ወይም ‹‹መርዝ ሰጥተውኛል›› ብሎ ያለጥርጥር ማመን። በማህበረሰቡ ዘንድ ከሚታመን ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ እምነት የተለየ ነው።
A firmly held belief that is not true and does not change even when there is clear evidence against it — for example, being certain of being followed or poisoned. It is different from a religious or cultural belief shared by one's community.
- ራስን የማጥፋት ሐሳብ Suicidal thoughts ሌሎች አጠራሮች፦ Suicidal ideation
-
የራስን ሕይወት ስለማጥፋት ማሰብ ነው፤ ‹‹ምነው ባልነቃሁ›› ከማለት ጀምሮ ዕቅድ እስከ ማውጣት ሊደርስ ይችላል። የከባድ ሥቃይ ምልክት እንጂ የኃጢአት ወይም የድክመት ምልክት አይደለም፤ ወዲያውኑ እርዳታ ለመጠየቅም በቂ ምክንያት ነው። አንድን ሰው ስለዚህ ሐሳብ በቀጥታ መጠየቅ ሐሳቡን አያስጀምርበትም።
Thoughts about ending one's own life, ranging from wishing not to wake up to making a plan. They are a sign of severe pain, not of sin or weakness, and they are a reason to reach out for help right away. Asking someone directly about suicide does not put the idea in their head.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ራስን መጉዳት Self-harm
-
ሆን ብሎ የራስን አካል መጉዳት ነው፤ ለምሳሌ መቁረጥ ወይም ማቃጠል። ብዙ ጊዜ ዓላማው መሞት ሳይሆን ከአቅም በላይ የሆነ ስሜትን ለመቋቋም መሞከር ነው። ሰውየው ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ምልክት ስለሆነ በቁም ነገር ሊታይ ይገባል።
Hurting one's own body on purpose, for example by cutting or burning, usually as a way to cope with overwhelming feelings rather than to die. It is a sign that a person needs support, and it should be taken seriously.
- መገለል Stigma ሌሎች አጠራሮች፦ ማግለልና አድልዎ
-
ሰዎች የአእምሮ ጤና ችግር ስላለባቸው ብቻ የሚደርስባቸው ማፈር፣ መወቀስ ወይም ፍትሐዊ ያልሆነ አያያዝ ነው፤ ለምሳሌ ሐሜት፣ ወይም ሕመሙን እንደ እርግማን ወይም የቤተሰብ ውርደት መቁጠር። መገለል ሰዎች ሕክምና እንዳይፈልጉ ያደርጋል፤ ትክክለኛ መረጃና ግልጽ ውይይት ግን ይቀንሰዋል።
Shame, blame, or unfair treatment directed at people because of a mental health condition — for example gossip, or treating illness as a curse or a family disgrace. Stigma keeps people from getting care; accurate information and open conversation reduce it.
የሕመም ስሞች · Names of conditions
- የአእምሮ ሕመም Mental illness ሌሎች አጠራሮች፦ የአእምሮ መታወክ · Mental disorder, Mental health condition
-
የአንድን ሰው አስተሳሰብ፣ ስሜት ወይም ባህሪ የሚነካና የዕለት ተዕለት ኑሮን የሚያከብድ የጤና ችግር ነው። እንደ ስኳር በሽታ ወይም የደም ግፊት ሁሉ ሕክምናዊ መንስኤና ሕክምና አለው፤ ቅጣት፣ እርግማን ወይም የባህሪ ጉድለት አይደለም።
A health condition that affects a person's thinking, feelings, mood, or behaviour and makes daily life harder. Like diabetes or high blood pressure, it has medical causes and treatments; it is not a punishment, a curse, or a character flaw.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ባይፖላር ዲስኦርደር Bipolar disorder ሌሎች አጠራሮች፦ የስሜት መዋዠቅ ሕመም
-
ከፍተኛ የስሜትና የጉልበት መለዋወጥን የሚያስከትል ሕመም ነው፤ የማኒያ (ከልክ ያለፈ መነቃቃት ወይም ቁጡነት) ጊዜያትና የድባቴ ጊዜያት ይፈራረቃሉ፤ በመካከላቸውም የተረጋጋ ጊዜ ይኖራል። በመድኃኒትና በንግግር ሕክምና ለረጅም ጊዜ ክትትል ይደረግለታል።
A condition that causes strong shifts in mood and energy: periods of mania (very high or irritable mood) and periods of depression, with stable times in between. It is managed long term with medication and therapy.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ስኪዞፈሪንያ Schizophrenia
-
አንድ ሰው የሚያስብበትን፣ የሚሰማውንና እውነታን የሚረዳበትን መንገድ የሚነካ ከባድና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሕመም ነው። ድምፅ መስማት፣ የተሳሳተ ጽኑ እምነትና ከሰው መራቅ ሊታዩ ይችላሉ። ‹‹የተከፈለ ስብዕና›› ማለት አይደለም። በሕክምናና በድጋፍ ብዙ ሰዎች የተረጋጋ ኑሮ ይኖራሉ።
A serious, long-term condition that affects how a person thinks, feels, and experiences reality. It can involve hearing voices, fixed false beliefs, and withdrawing from others. It does not mean a "split personality". With treatment and support many people live stable lives.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ድህረ-አሰቃቂ ጭንቀት (PTSD) Post-traumatic stress disorder (PTSD) ሌሎች አጠራሮች፦ ከአሰቃቂ ገጠመኝ በኋላ የሚከሰት የጭንቀት ሕመም
-
እጅግ አስፈሪ ገጠመኝ ካለፈ በኋላ ሊከሰት የሚችል ሕመም ነው። ከአንድ ወር በላይ ሰውየው ገጠመኙን በትዝታ ወይም በሕልም ደጋግሞ ይኖረዋል፣ የሚያስታውሱትን ነገሮች ይሸሻል፣ ሁልጊዜ በተጠንቀቅ ይሆናል፣ የስሜት ለውጥም ይታይበታል። የሚታከም ሕመም ነው።
A condition that can develop after a terrifying event. For more than a month the person relives the event in memories or nightmares, avoids reminders, feels constantly on guard, and has changes in mood. It is treatable.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ኦ.ሲ.ዲ (OCD) Obsessive-compulsive disorder (OCD) ሌሎች አጠራሮች፦ አስጨናቂ ሐሳብና ተደጋጋሚ ድርጊት ሕመም
-
ሳይፈልጉት ደጋግሞ የሚመጣ አስጨናቂ ሐሳብ (ኦብሰሽን) እና ጭንቀቱን ለማቃለል ደጋግሞ ለመፈጸም የሚገደዱበት ድርጊት (ኮምፐልሽን) ያለበት ሕመም ነው፤ ለምሳሌ ደጋግሞ መታጠብ ወይም ደጋግሞ ማረጋገጥ። ብዙ ጊዜ ይወስዳል፤ በሕክምናም ይሻሻላል።
A condition with unwanted, upsetting thoughts that keep coming back (obsessions) and actions a person feels driven to repeat to ease the distress (compulsions), such as repeated washing or checking. It takes up a lot of time and is treatable.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የትኩረት ማጣትና የመቅበጥበጥ ችግር (ADHD) Attention-deficit/hyperactivity disorder (ADHD) ሌሎች አጠራሮች፦ የትኩረት ጉድለት ዲስኦርደር
-
ከልጅነት የሚጀምር ሲሆን ትኩረት መስጠትን፣ ረግቶ መቀመጥን ወይም ስሜትን መቆጣጠርን ለዕድሜው ከሚጠበቀው በላይ የሚያከብድ ችግር ነው። በወላጆች አስተዳደግ ጉድለት ወይም በስንፍና የሚመጣ አይደለም፤ እስከ አዋቂነትም ሊቀጥል ይችላል።
A condition that begins in childhood and makes it hard to pay attention, sit still, or control impulses, more than is usual for the person's age. It is not caused by bad parenting or laziness, and it can continue into adulthood.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ኦቲዝም Autism spectrum disorder
-
ከሕፃንነት ጀምሮ የሚታይ የዕድገት ሁኔታ ሲሆን አንድ ሰው የሚግባባበትን፣ ከሌሎች ጋር የሚቀራረብበትንና ዓለምን የሚረዳበትን መንገድ ይነካል። በክትባት፣ በአስተዳደግ ወይም በመንፈሳዊ ኃይል የሚመጣ አይደለም። ቀደም ብሎ የሚሰጥ ድጋፍ ልጆች እንዲማሩና እንዲያድጉ ይረዳል።
A developmental condition, present from early childhood, that affects how a person communicates, relates to others, and experiences the world. It is not caused by vaccines, parenting, or spiritual forces. Early support helps children learn and thrive.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የስብዕና መዛባት Personality disorder ሌሎች አጠራሮች፦ የስብዕና መታወክ
-
ከማህበረሰቡ ከሚጠበቀው በእጅጉ የተለየ፣ ከወጣትነት ጀምሮ የሚታይና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የአስተሳሰብ፣ የስሜትና ከሰዎች ጋር የመግባባት ዘይቤ ነው፤ ለሰውየው ሥቃይ ወይም በግንኙነትና በሥራ ላይ ችግር ያስከትላል።
A long-standing pattern of thinking, feeling, and relating to others that differs markedly from what is expected in the person's culture, begins by early adulthood, and causes distress or problems in relationships and work.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ሂስትሪዮኒክ ስብዕና መዛባት Histrionic personality disorder ሌሎች አጠራሮች፦ ከልክ ያለፈ ትኩረት ፈላጊነት የሚታይበት የስብዕና መዛባት
-
ከፍተኛ የስሜት ገላጭነት፣ ድራማዊ ባህሪና የሰዎችን ትኩረት የመሳብ ጠንካራ ፍላጎት የሚታይበት የስብዕና መዛባት ነው። ‹‹ሂስትሪዮኒክ›› ማለት ‹‹ትወና መሰል›› ማለት ነው፤ ከ‹‹ታሪክ›› ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።
A personality disorder marked by very emotional, dramatic behaviour and a strong need to be the centre of attention. "Histrionic" means theatrical; it has nothing to do with history.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የድንበር (ቦርደርላይን) ስብዕና መታወክ Borderline personality disorder ሌሎች አጠራሮች፦ ቦርደርላይን
-
ሰው ስሜቱን የሚቆጣጠርበትን፣ ራሱን የሚያይበትንና ግንኙነቶቹን የሚጠብቅበትን መንገድ የሚነካ ሕመም ነው። ብዙ ጊዜ ጠንካራና በፍጥነት የሚቀያየር ስሜት፣ የመተው ፍርሃት እንዲሁም በግብታዊነት ወይም ራስን በመጉዳት የሚገለጽ ባህሪ ይታይበታል። እንደ DBT ያሉ የንግግር ሕክምናዎች ብዙ ሰዎች እንዲሻሻሉ ይረዳሉ።
A condition that affects how a person manages emotions, sees themselves and keeps relationships. It often brings intense, fast-changing moods, fear of being abandoned, and impulsive or self-harming behaviour. Talk therapies such as DBT help many people improve.
ተጨማሪ ያንብቡ → - አቮይዳንት ስብዕና መዛባት Avoidant personality disorder ሌሎች አጠራሮች፦ ሰዎችን የመሸሽ ስብዕና መዛባት
-
ከልጅነት ጀምሮ የሚቀጥል ከፍተኛ ዓይናፋርነት፣ ‹‹ብቁ አይደለሁም›› የሚል ስሜትና ተቀባይነት ማጣትን አጥብቆ መፍራት የሚታይበት የስብዕና መዛባት ነው፤ ሰውየው በዚህ ምክንያት ከሰዎችና ከአዳዲስ ነገሮች ይሸሻል።
A personality disorder marked by lifelong, intense shyness, feeling inadequate, and being so sensitive to rejection that the person avoids people and new activities.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ናርሲሲስቲክ ስብዕና መታወክ Narcissistic personality disorder ሌሎች አጠራሮች፦ ከልክ ያለፈ ራስን የማግዘፍ ስብዕና መዛባት
-
ራስን ከልክ በላይ ከፍ አድርጎ ማየት፣ የሌሎችን አድናቆት አጥብቆ መፈለግና የሌሎችን ስሜት ለመረዳት መቸገር የሚታይበት የስብዕና መዛባት ነው።
A personality disorder marked by an exaggerated sense of self-importance, a strong need for admiration, and difficulty recognising other people's feelings.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ኦብሰሲቭ-ኮምፐልሲቭ ስብዕና መዛባት (OCPD) Obsessive-compulsive personality disorder (OCPD)
-
ለሥርዓት፣ ለደንብ፣ ለቁጥጥርና ለፍጽምና ከፍተኛ ፍላጎት የሚታይበት የስብዕና መዛባት ሲሆን ሥራን ለመጨረስና ከሰዎች ጋር ለመግባባት እንቅፋት ይሆናል። ከኦ.ሲ.ዲ (OCD) የተለየ ሕመም ነው።
A personality disorder marked by a strong need for order, rules, control, and perfection, to the point that it gets in the way of finishing tasks and of relationships. It is a different condition from OCD.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የሱስ ሕመም Substance use disorder ሌሎች አጠራሮች፦ ሱስ፣ የቁስ አጠቃቀም ችግር · Addiction
-
አንድ ሰው አልኮል፣ ጫት ወይም ሌላ አደንዛዥ ዕፅ ጤናውን፣ ሥራውን ወይም ቤተሰቡን እየጎዳ እያለም መጠቀሙን የሚቀጥልበትና ለማቆም በጣም የሚቸገርበት ሕመም ነው። የሚታከም ሕመም እንጂ የሥነ ምግባር ውድቀት አይደለም።
A medical condition in which a person keeps using alcohol, khat, or other drugs even though it harms their health, work, or family, and finds it very hard to stop. It is treatable, and it is not a moral failing.
ተጨማሪ ያንብቡ → - ናርኮሌፕሲ Narcolepsy ሌሎች አጠራሮች፦ በአንጎል የሚከሰት የእንቅልፍ ቁጥጥር ችግር
-
አንጎል እንቅልፍንና ንቃትን በተለመደው መንገድ መቆጣጠር የማይችልበት፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የነርቭ ሥርዓት ችግር ነው፤ በዚህም ምክንያት ሰውየው ባልተጠበቀ ጊዜና ቦታ ከባድ የእንቅልፍ ስሜት ይሰማዋል ወይም ይተኛል።
A long-term neurological condition in which the brain cannot regulate sleep and wakefulness normally, so a person becomes very drowsy or falls asleep at unexpected times and places.
Read more (English) →
ሕክምናና እንክብካቤ · Treatment and care
- ቅድመ ምርመራ Screening ሌሎች አጠራሮች፦ ስክሪኒንግ
-
አንድ ሰው እንደ ድባቴ ያለ ሕመም ሊኖርበት ይችል እንደሆነ ለማወቅ የሚቀርቡ ጥቂት ጥያቄዎች ናቸው። ቅድመ ምርመራ የመጨረሻ የሕመም ልየታ አይደለም፤ ዝርዝር ምርመራ ያስፈልግ እንደሆነ ብቻ ያሳያል።
A short set of questions that checks whether a person may have a condition such as depression. A screening is not a diagnosis; it shows whether a fuller assessment is worthwhile.
Read more (English) → - የሕመም ልየታ Diagnosis ሌሎች አጠራሮች፦ ምርመራ፣ ዲያግኖሲስ
-
የጤና ባለሙያ ከሰውየው ጋር በመነጋገርና አንዳንዴም በምርመራ ታግዞ የምልክቶቹ መንስኤ የትኛው ሕመም እንደሆነ የሚደርስበት ድምዳሜ ነው። የሕመም ልየታ ተገቢውን ሕክምና ለመምረጥ መነሻ እንጂ የዕድሜ ልክ መለያ አይደለም።
A health professional's conclusion about which condition explains a person's symptoms, reached by talking with the person and sometimes with tests. A diagnosis is a starting point for choosing treatment, not a label for life.
- የንግግር ሕክምና Psychotherapy ሌሎች አጠራሮች፦ ሳይኮቴራፒ፣ የምክር አገልግሎት · Talk therapy, Counseling
-
ከሠለጠነ ባለሙያ ጋር በመደበኛነትና በሚስጥር በሚደረግ ውይይት የሚሰጥ ሕክምና ነው፤ ስሜትን ለመረዳትና ችግርን የመቋቋሚያ ተግባራዊ ዘዴዎችን ለመማር ይረዳል። ከጓደኛ ወይም ከሽማግሌ ምክር የተለየ ነው፤ በጥናት የተረጋገጡ ዘዴዎችን ይከተላል፣ ሚስጥርም ይጠበቃል።
Treatment through regular, private conversations with a trained professional, to understand feelings and learn practical ways of coping. It is different from advice from a friend or elder: it follows tested methods and is confidential.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የአስተሳሰብና የባህሪ ሕክምና (CBT) Cognitive behavioral therapy (CBT) ሌሎች አጠራሮች፦ ኮግኒቲቭ ቢሄቪየራል ቴራፒ
-
አንድ ሰው የማይጠቅሙ የአስተሳሰብና የባህሪ ልማዶቹን እንዲለይና በተሻሉ እንዲተካ የሚረዳ፣ በሥርዓት የተዋቀረና ብዙ ጊዜ ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ የንግግር ሕክምና ነው። ለድባቴና ለጭንቀት በስፋት ከተጠኑ ሕክምናዎች አንዱ ነው።
A structured, usually short-term talk therapy that helps a person notice unhelpful patterns of thinking and behaviour and practise more helpful ones. It is one of the best-studied treatments for depression and anxiety.
ተጨማሪ ያንብቡ → - መድኃኒት Medication ሌሎች አጠራሮች፦ መድሃኒት
-
ምልክቶችን ለመቀነስ በሐኪም ወይም ፈቃድ ባለው ባለሙያ የሚታዘዝ ነው። የአእምሮ ጤና መድኃኒቶች ብዙ ጊዜ ውጤት ለማሳየት ብዙ ሳምንታት ይወስዳሉ፤ ያዘዘውን ባለሙያ ሳያማክሩ በድንገት ማቆምም አይገባም።
Medicine prescribed by a doctor or other licensed prescriber to reduce symptoms. Mental health medications often take several weeks to work and should not be stopped suddenly without talking to the prescriber.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የድባቴ መድኃኒት Antidepressant ሌሎች አጠራሮች፦ ፀረ-ድባቴ መድኃኒት
-
ድባቴንና አንዳንድ የጭንቀት ሕመሞችን ለማከም የሚያገለግል መድኃኒት ነው። ሙሉ ውጤቱ እስኪታይ ብዙ ሳምንታት (ብዙ ጊዜ ከአራት እስከ ስምንት) ይወስዳል። እንደ አልኮል ወይም እንደ አንዳንድ ማረጋጊያ መድኃኒቶች ሱስ አያስይዝም፤ ሆኖም በድንገት ማቆም አይገባም፤ በሐኪም ምክር ቀስ በቀስ መቀነስ አለበት።
A medication used to treat depression and also some anxiety conditions. It usually takes several weeks (often four to eight) to feel the full effect. Antidepressants do not cause addiction the way alcohol or some sedatives can, but they should be reduced gradually with a doctor's guidance rather than stopped suddenly.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የሳይኮሲስ መድኃኒት Antipsychotic ሌሎች አጠራሮች፦ አንቲሳይኮቲክ፣ ፀረ-ሳይኮሲስ መድኃኒት
-
እንደ ድምፅ መስማት ወይም የተሳሳተ ጽኑ እምነት ያሉ የሳይኮሲስ ምልክቶችን የሚቀንስ መድኃኒት ነው። ለስኪዞፈሪንያ፣ ለባይፖላር ዲስኦርደር፣ አንዳንዴም ለከባድ ድባቴ ከሌላ ሕክምና ጋር ይሰጣል።
A medication that reduces symptoms of psychosis such as hearing voices or fixed false beliefs. It is used for schizophrenia, for bipolar disorder, and sometimes alongside other treatment for severe depression.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የስሜት ማረጋጊያ መድኃኒት Mood stabilizer
-
ከልክ ያለፈ የስሜት ከፍታና ዝቅታን የሚያመጣጥን መድኃኒት ሲሆን በዋናነት ለባይፖላር ዲስኦርደር ይሰጣል። አንዳንዶቹ መደበኛ የደም ምርመራ ያስፈልጋቸዋል።
A medication that evens out extreme highs and lows of mood, used mainly for bipolar disorder. Some mood stabilizers need regular blood tests.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የጎንዮሽ ጉዳት Side effect
-
መድኃኒት ከሚሰጠው ጥቅም ጎን የሚያስከትለው ያልተፈለገ ውጤት ነው፤ ለምሳሌ ማቅለሽለሽ፣ እንቅልፍ ማብዛት ወይም የክብደት ለውጥ። ብዙዎቹ ከመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በኋላ ይቀንሳሉ። መድኃኒቱን ላዘዘልዎት ባለሙያ ይንገሩ፤ ብዙ ጊዜ መጠኑን ወይም መድኃኒቱን መቀየር ይቻላል።
An unwanted effect of a medication, such as nausea, sleepiness, or weight change. Many side effects ease after the first weeks. Tell the prescriber about them — the dose or the medicine can often be changed.
- ማገርሸት Relapse
-
ለተወሰነ ጊዜ ከተሻለ በኋላ የሕመሙ ምልክቶች መመለስ ነው። በብዙ ሕመሞች ላይ የሚያጋጥም ነው፤ ውድቀትም አይደለም። ከጤና ባለሙያ ጋር ተገናኝቶ የሕክምና ዕቅዱን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ምልክት ነው።
The return of symptoms after a period of feeling better. Relapse is common in many conditions and is not a failure; it is a signal to contact the care provider and adjust the plan.
- ማገገም Recovery
-
አንዳንድ ምልክቶች ቢቀሩም ባይቀሩም እየተሻሉ መሄድና ትርጉም ያለው ሕይወት መገንባት ነው። ማገገም ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ መልክ አለው፤ ብዙ ጊዜም ሕክምናን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብንና እምነትን ያካትታል።
The process of getting better and building a meaningful life, with or without some remaining symptoms. Recovery looks different for each person and often includes treatment, family, community, and faith.
- ራስን መንከባከብ Self-care
-
የአእምሮንና የአካልን ጤና የሚጠብቁ የዕለት ተዕለት ልማዶች ናቸው፤ በቂ እንቅልፍ፣ በሰዓቱ መመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ፣ ከሚደግፉን ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ ጸሎት ወይም ማሰላሰል እና ዕረፍት። ራስን መንከባከብ ሕክምናን ያግዛል እንጂ ምልክቶች ሲከብዱ ሕክምናን አይተካም።
Everyday habits that protect mental and physical health: sleep, regular meals, movement, time with people who support you, prayer or reflection, and rest. Self-care supports treatment; it does not replace it when symptoms are serious.
Read more (English) → - የአእምሮ ጤና ቀውስ Mental health crisis
-
የአንድ ሰው ሐሳብ፣ ስሜት ወይም ባህሪ ራሱን ወይም ሌሎችን ለጉዳት የሚያጋልጥበት፣ ወይም ራሱን መንከባከብ የማይችልበት ሁኔታ ነው። ቀውስ አሁኑኑ እርዳታ ይፈልጋል፤ ከቀውስ የስልክ መስመር፣ ከአደጋ ጊዜ ስልክ ቁጥር ወይም በአቅራቢያ ካለ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል።
A situation in which a person's thoughts, feelings, or behaviour put them or others at risk of harm, or leave them unable to care for themselves. A crisis needs help now — from a crisis line, an emergency number, or the nearest emergency room.
ተጨማሪ ያንብቡ →
ባለሙያዎች · Who is who
- የአእምሮ ሐኪም Psychiatrist ሌሎች አጠራሮች፦ ሳይካትሪስት
-
በአእምሮ ጤና ላይ ስፔሻላይዝ ያደረገ የሕክምና ዶክተር ነው። ሕመምን ይለያል፣ መድኃኒት ያዝዛል፣ አንዳንዴም የንግግር ሕክምና ይሰጣል።
A medical doctor who specialises in mental health. A psychiatrist can diagnose conditions, prescribe medication, and sometimes provide talk therapy.
- የሥነ ልቦና ባለሙያ Psychologist ሌሎች አጠራሮች፦ ሳይኮሎጂስት
-
ሰዎች እንዴት እንደሚያስቡ፣ እንደሚሰማቸውና እንደሚያደርጉ ከፍተኛ ሥልጠና የወሰደ ባለሙያ ነው። ምዘናና የንግግር ሕክምና ይሰጣል፤ በአብዛኛው ቦታ መድኃኒት አያዝዝም።
A professional with advanced training in how people think, feel, and behave. A psychologist provides assessment and talk therapy; in most places psychologists do not prescribe medication.
- ቴራፒስት Therapist ሌሎች አጠራሮች፦ የንግግር ሕክምና ባለሙያ፣ አማካሪ · Counselor, Clinical social worker
-
የንግግር ሕክምና ለሚሰጥ ፈቃድ ያለው ባለሙያ የሚሰጥ አጠቃላይ መጠሪያ ነው፤ አማካሪ፣ ክሊኒካል ማህበራዊ ሠራተኛ፣ የሥነ ልቦና ባለሙያ ወይም የትዳርና የቤተሰብ ቴራፒስት ሊሆን ይችላል።
A general word for a licensed professional who provides talk therapy, such as a counselor, clinical social worker, psychologist, or marriage and family therapist.
ተጨማሪ ያንብቡ → - የሕክምና አስተርጓሚ Medical interpreter ሌሎች አጠራሮች፦ አስተርጓሚ
-
በታካሚና በጤና ባለሙያ መካከል በአካል፣ በስልክ ወይም በቪዲዮ የሚያስተረጉም የሠለጠነ ሰው ነው። የሕክምና አስተርጓሚ የሰማውን በሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ አለበት፤ ታካሚዎችም ልጆቻቸውን ወይም ዘመዶቻቸውን ለአስተርጓሚነት እንዲጠቀሙ መገደድ የለባቸውም።
A trained person who translates between a patient and a health professional, in person, by phone, or by video. Medical interpreters must keep what they hear confidential, and patients should not have to rely on children or relatives to interpret.
ተጨማሪ ያንብቡ →
ግላዊነትና መብት · Privacy and rights
- ሚስጥር መጠበቅ Confidentiality ሌሎች አጠራሮች፦ ምስጢራዊነት፣ ግላዊነት · Privacy
-
የጤና ባለሙያዎችና አስተርጓሚዎች ታካሚ የነገራቸውን በሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ነው። ያለ ታካሚው ፈቃድ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ አባላት ወይም ለአሠሪ መንገር አይችሉም፤ ለሕይወት አስቸኳይ አደጋ እንዳለ ባሉ ውስን ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር።
The duty of health professionals and interpreters to keep what a patient tells them private. They may not share it with family, community members, or employers without the patient's permission, except in limited situations such as an immediate danger to life.
ተጨማሪ ያንብቡ → - በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፈቃድ Informed consent
-
የሕክምናው ጥቅም፣ ጉዳትና ሌሎች አማራጮች በሚገባው ቋንቋ ከተብራሩለት በኋላ ታካሚው ለሕክምናው የሚሰጠው ስምምነት ነው። ታካሚ ጥያቄ የመጠየቅ፣ ጊዜ ወስዶ የማሰብና ‹‹አልፈልግም›› የማለት መብት አለው።
A patient's agreement to a treatment after the benefits, risks, and alternatives have been explained in a language they understand. A patient has the right to ask questions, to take time, and to say no.