ኦቲዝም
የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር (ASD) ሰዎች ከሌሎች ጋር በሚገናኙበት፣ በሚግባቡበት፣ በሚማሩበትና በሚያሳዩት ባህሪ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር የነርቭና የዕድገት መታወክ ነው። ኦቲዝም በማንኛውም ዕድሜ ሊታወቅ ቢችልም ምልክቶቹ በአብዛኛው በሕይወት የመጀመሪያዎቹ 2 ዓመታት ውስጥ ስለሚታዩ ‹‹የዕድገት መታወክ›› ተብሎ ይጠራል።
የጤና ባለሙያዎች የአእምሮ መታወክን ለመመርመር የሚጠቀሙበትና በአሜሪካ የሥነ አእምሮ ሐኪሞች ማኅበር የተዘጋጀው የአእምሮ መታወኮች የምርመራና የስታቲስቲክስ መመሪያ (DSM-5) እንደሚለው፣ ASD ያለባቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚከተሉት ይታዩባቸዋል፦
- ከሌሎች ሰዎች ጋር የመግባባትና የመገናኘት ችግር
- ውስን (በጥቂት ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮሩ) ፍላጎቶችና ተደጋጋሚ ባህሪያት
- በትምህርት ቤት፣ በሥራና በሌሎች የሕይወት ዘርፎች ተግባራቸውን የመወጣት ችሎታቸውን የሚነኩ ምልክቶች
ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ምልክቶች ዓይነትና ክብደት ከሰው ሰው በእጅጉ ስለሚለያይ ኦቲዝም ‹‹ስፔክትረም›› (ሰፊ ክልል ያለው) መታወክ ተብሎ ይጠራል።
ከየትኛውም ፆታ፣ ዘር፣ ብሔረሰብና የኢኮኖሚ ደረጃ የመጡ ሰዎች ASD እንዳለባቸው ሊታወቅ ይችላል። ASD ዕድሜ ልክ የሚቆይ ሊሆን ቢችልም ሕክምናና አገልግሎቶች የሰውየውን ምልክቶችና የዕለት ተዕለት ኑሮውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ። የአሜሪካ የሕፃናት ሐኪሞች አካዳሚ ሁሉም ልጆች የኦቲዝም ቅድመ ምርመራ (screening) እንዲደረግላቸው ይመክራል። ወላጆችና አሳዳጊዎች ስለ ASD ቅድመ ምርመራ ወይም ግምገማ የልጃቸውን ሐኪም ማነጋገር አለባቸው።
የASD ምልክቶች
ከዚህ በታች ያለው ዝርዝር ASD እንዳለባቸው በታወቀ ሰዎች ላይ በብዛት የሚታዩ ባህሪያትን በምሳሌነት ያቀርባል። ASD ያለበት እያንዳንዱ ሰው ሁሉንም ባህሪያት አያሳይም፤ አብዛኞቹ ግን ከተዘረዘሩት ውስጥ በርከት ያሉትን ያሳያሉ።
በመግባባትና ከሰዎች ጋር በመገናኘት ረገድ የሚታዩ ባህሪያት
- ሰዎችን ዓይን ለዓይን ብዙም አለማየት ወይም አልፎ አልፎ ብቻ ማየት
- የሚያናግሯቸውን ሰዎች የማያዩ ወይም የማይሰሙ መምሰል
- በአንድ ነገር ወይም ተግባር ላይ ያላቸውን ፍላጎት፣ ስሜት ወይም ደስታ ለሌሎች እምብዛም አለማጋራት (ለምሳሌ ነገሮችን በጣት እምብዛም አለመጠቆም ወይም ለሌሎች አለማሳየት)
- ስማቸው ሲጠራ ወይም ትኩረታቸውን ለመሳብ ሲነገራቸው ምላሽ አለመስጠት ወይም ዘግይተው መመለስ
- በተራ እየተነጋገሩ ውይይትን የማስቀጠል ችግር
- ሌሎች ፍላጎት እንደሌላቸው ሳያስተውሉ ወይም ሌሎች እንዲመልሱ ዕድል ሳይሰጡ ስለሚወዱት ርዕስ ብዙ ጊዜ በረጅሙ መናገር
- ከሚናገሩት ነገር ጋር የማይስማማ የፊት ገጽታ፣ እንቅስቃሴ ወይም የእጅ ምልክት ማሳየት
- እንደ ዜማ የሚወጣና የሚወርድ ወይም ስሜት የሌለው፣ ሮቦት የሚመስል ያልተለመደ የድምፅ ቃና
- የሌላውን ሰው አመለካከት ለመረዳት መቸገር ወይም የሌሎችን ድርጊት አስቀድሞ መገመት ወይም መረዳት አለመቻል
- ባህሪን ከሁኔታውና ከአካባቢው ጋር ለማስማማት መቸገር
- በምናብ (በ‹‹እንደ›› ጨዋታ) አብሮ ለመጫወት ወይም ጓደኛ ለማፍራት መቸገር
ውስን ፍላጎቶችና ተደጋጋሚ ባህሪያት
- አንዳንድ ባህሪያትን ደጋግሞ ማድረግ ወይም ያልተለመደ ባህሪ ማሳየት፤ ለምሳሌ ቃላትን ወይም ሐረጎችን መደጋገም (ኢኮላሊያ (echolalia) የሚባል ባህሪ)
- እንደ ቁጥሮች፣ ዝርዝር ነገሮች ወይም እውነታዎች ባሉ የተወሰኑ ርዕሶች ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ከፍተኛ ፍላጎት
- በአንድ ነገር ላይ ከልክ በላይ ማተኮር፤ ለምሳሌ በሚንቀሳቀሱ ነገሮች ወይም በአንድ ዕቃ የተወሰነ ክፍል ላይ
- በተለመደው የዕለት ተግባር ላይ ትንሽ ለውጥ ሲደረግ መበሳጨትና ከአንድ ተግባር ወደ ሌላው ለመሸጋገር መቸገር
- እንደ ብርሃን፣ ድምፅ፣ ልብስ ወይም ሙቀት ላሉ በስሜት ሕዋሳት ለሚሰሙ ነገሮች ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ወይም ያነሰ ተጋላጭ (ስሱ) መሆን
ASD ያለባቸው ሰዎች የእንቅልፍ ችግርና ቁጡነት (በቀላሉ መበሳጨት) ሊያጋጥማቸው ይችላል።
በኦቲዝም ስፔክትረም ውስጥ ያሉ ሰዎችም ብዙ ጥንካሬዎች ሊኖራቸው ይችላል፣ ከእነዚህም መካከል፡-
- ነገሮችን በዝርዝር መማር እና መረጃን ለረጅም ጊዜ ማስታወስ መቻል
- በማየትና በመስማት በደንብ የመማር ችሎታ
- በሂሳብ፣ በሳይንስ፣ በሙዚቃ ወይም በሥነ ጥበብ የላቀ ችሎታ ማሳየት
መንስኤዎች እና ተዛማጅ ምክንያቶች
ተመራማሪዎች የASD ዋና መንስኤዎችን እስካሁን አያውቁም። ጥናቶች ግን የሰው ጂኖች ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር ተጣምረው ዕድገትን ወደ ASD በሚያመሩ መንገዶች ሊነኩ እንደሚችሉ ያመለክታሉ። ASD የመከሰት ዕድልን ከፍ ከማድረግ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- ASD ያለበት ወንድም ወይም እህት መኖር
- በዕድሜ የገፉ ወላጆች መኖር
- አንዳንድ የጄኔቲክ ሁኔታዎች መኖር (እንደ ዳውን ሲንድሮም ወይም ፍራጊል ኤክስ ሲንድሮም)
- ሲወለዱ ክብደታቸው በጣም ዝቅተኛ መሆን
ኦቲዝም (ASD) እንዴት ይታወቃል?
የጤና ባለሙያዎች ASDን የሚለዩት የሰውየውን ባህሪና ዕድገት በመገምገም ነው። ASD በአብዛኛው ልጁ 2 ዓመት ሲሞላው በአስተማማኝ ሁኔታ ሊታወቅ ይችላል። በተቻለ ፍጥነት ግምገማ ማስደረግ አስፈላጊ ነው፤ ASD ቶሎ በታወቀ ቁጥር ሕክምናና አገልግሎቶችም ቶሎ ሊጀመሩ ይችላሉ።
በትናንሽ ልጆች ላይ የሚደረግ ምርመራ
በትናንሽ ልጆች ላይ የሚደረገው ምርመራ ብዙ ጊዜ በሁለት ደረጃዎች ይከናወናል።
ደረጃ 1፦ በመደበኛ የልጅ ጤና ክትትል ወቅት የሚደረግ አጠቃላይ የዕድገት ቅድመ ምርመራ
እያንዳንዱ ልጅ በሕፃናት ሐኪም ወይም በሕፃናት ጤና ባለሙያ መደበኛ የጤና ክትትል ሊደረግለት ይገባል። የአሜሪካ የሕፃናት ሐኪሞች አካዳሚ ሁሉም ልጆች በ9፣ በ18 እና በ24 ወይም በ30 ወር የጤና ክትትል ጉብኝታቸው የዕድገት መዘግየት ቅድመ ምርመራ እንዲደረግላቸው፣ በ18 እና በ24 ወር ጉብኝታቸው ደግሞ የተለየ የኦቲዝም ቅድመ ምርመራ እንዲደረግላቸው ይመክራል። አንድ ልጅ ASD ወይም የዕድገት ችግር የመያዝ ዕድሉ ከፍ ያለ ከሆነ ተጨማሪ ቅድመ ምርመራ ሊደረግለት ይችላል። ASD የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ልጆች ASD ያለበት የቤተሰብ አባል ያላቸው፣ የASD ዓይነተኛ ባህሪያትን የሚያሳዩ፣ በዕድሜ የገፉ ወላጆች ያሏቸው፣ የተወሰኑ የዘረመል ሁኔታዎች ያሉባቸው ወይም ሲወለዱ ክብደታቸው በጣም ዝቅተኛ የነበረ ልጆች ናቸው።
የወላጆችንና የአሳዳጊዎችን ተሞክሮና ስጋት ግምት ውስጥ ማስገባት በትናንሽ ልጆች ቅድመ ምርመራ ውስጥ አስፈላጊ አካል ነው። ሐኪሙ ስለ ልጁ ባህሪ ጥያቄዎችን ሊጠይቅና መልሶቹን ከASD ቅድመ ምርመራ መሣሪያዎችና ልጁን በቀጥታ ከመከታተል ከሚያገኘው መረጃ ጋር አጣምሮ ሊገመግም ይችላል። ስለ ቅድመ ምርመራ መሣሪያዎች በበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ድረ-ገጽ ላይ የበለጠ ያንብቡ።
በዚህ የቅድመ ምርመራ ሂደት አንድ ልጅ በባህሪው ወይም በዕለት ተግባሩ የዕድገት ልዩነት ካሳየ ሐኪሙ ልጁን ለተጨማሪ ግምገማ ወደ ሌላ ባለሙያ ሊልከው ይችላል።
ደረጃ 2፦ ተጨማሪ የምርመራ ግምገማ
ASD ያለባቸውን ልጆች በተቻለ ፍጥነት በትክክል መለየትና መመርመር አስፈላጊ ነው፤ ይህ የልጆቹን ልዩ ጥንካሬዎችና ተግዳሮቶች ለመረዳት ይረዳል። ቶሎ መለየት ወላጆችና አሳዳጊዎች የትኞቹ አገልግሎቶች፣ የትምህርት ፕሮግራሞችና የባህሪ ሕክምናዎች ለልጃቸው ይበልጥ ሊጠቅሙ እንደሚችሉ እንዲወስኑም ያግዛቸዋል።
ASDን በመመርመር ልምድ ያላቸው የጤና ባለሙያዎች ቡድን የምርመራውን ግምገማ ያካሂዳል። ቡድኑ የሕፃናት ነርቭ ሐኪሞችን፣ በሕፃናት ዕድገት ላይ የተሰማሩ የሕፃናት ሐኪሞችን፣ የንግግርና የቋንቋ ቴራፒስቶችን፣ የሕፃናት ሳይኮሎጂስቶችንና የሥነ አእምሮ ሐኪሞችን፣ የትምህርት ባለሙያዎችንና የሙያ ቴራፒስቶችን (occupational therapists) ሊያካትት ይችላል።
የምርመራው ግምገማ የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፦
- የአካልና የነርቭ ምርመራዎች
- የልጁን የማሰብና የመረዳት (cognitive) ችሎታዎች መገምገም
- የልጁን የቋንቋ ችሎታዎች መገምገም
- የልጁን ባህሪ መከታተል
- ስለ ልጁ ባህሪና ዕድገት ከወላጆቹ ወይም ከአሳዳጊዎቹ ጋር ጥልቅ ውይይት
- እንደ መብላት፣ ልብስ መልበስና መጸዳጃ ቤት መጠቀም ያሉ የዕለት ተግባራትን ያለ ሌላ ሰው እርዳታ ለማከናወን የሚያስፈልጉ ከዕድሜው ጋር የሚመጣጠኑ ክህሎቶችን መገምገም
ASD አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች ሕመሞች ወይም የመማር ችግሮች ጋር አብሮ የሚከሰት ውስብስብ መታወክ ስለሆነ፣ አጠቃላይ ግምገማው የሚከተሉትንም ሊያካትት ይችላል፦
- የደም ምርመራዎች
- የመስማት ችሎታ ምርመራ
ግምገማው ወደ ይፋዊ የምርመራ ውጤት (diagnosis) እና የሕክምና ምክሮች ሊያደርስ ይችላል።
በትልልቅ ልጆችና በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚደረግ ምርመራ
ትምህርት ቤት በሚማሩ ትልልቅ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ላይ የASD ምልክቶችን ቀድመው የሚያስተውሉት ብዙ ጊዜ ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና መምህራን ናቸው። የትምህርት ቤቱ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቡድን የመጀመሪያ ግምገማ አድርጎ ልጁ በቤተሰብ ሐኪሙ ወይም በASD ላይ በተሰማራ ባለሙያ ተጨማሪ ግምገማ እንዲደረግለት ሊመክር ይችላል።
ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጃቸው ከሰዎች ጋር ስለሚገጥመው ችግር፣ በግልጽ በማይነገሩ የመግባቢያ ፍንጮች ላይ ያለውን ችግር ጨምሮ፣ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ። ለምሳሌ አንዳንድ ልጆች የድምፅ ቃናን፣ የፊት ገጽታን ወይም የሰውነት እንቅስቃሴን ትርጉም ለመረዳት ይቸገራሉ። ትልልቅ ልጆችና ታዳጊ ወጣቶች ፈሊጣዊ አነጋገርን፣ ቀልድን ወይም ሽሙጥን ለመረዳት ሊቸገሩ ይችላሉ። ከእኩዮቻቸው ጋር ጓደኝነት ለመመሥረትም ሊቸገሩ ይችላሉ።
በአዋቂዎች ላይ የሚደረግ ምርመራ
በአዋቂዎች ላይ ASDን መለየት ብዙ ጊዜ በልጆች ላይ ከመለየት የበለጠ ከባድ ነው። በአዋቂዎች አንዳንድ የASD ምልክቶች እንደ የጭንቀት መታወክ ወይም የትኩረት ማጣትና ከልክ ያለፈ እንቅስቃሴ መታወክ (ADHD) ካሉ የሌሎች የአእምሮ ጤና መታወኮች ምልክቶች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ።
በራሳቸው ላይ የASD ምልክቶችን ያስተዋሉ አዋቂዎች ሐኪማቸውን አነጋግረው ለASD ግምገማ ወደ ሌላ ባለሙያ እንዲላኩ (referral) መጠየቅ አለባቸው። በአዋቂዎች ላይ የሚደረገው የASD ግምገማ ገና እየዳበረ ያለ ቢሆንም፣ አዋቂዎች በASD ልምድ ወዳለው ኒውሮሳይኮሎጂስት፣ ሳይኮሎጂስት ወይም የሥነ አእምሮ ሐኪም ሊላኩ ይችላሉ። ባለሙያው ስለሚከተሉት ይጠይቃል፦
- ከሰዎች ጋር በመገናኘትና በመግባባት ላይ ያሉ ችግሮች
- ከስሜት ሕዋሳት (ብርሃን፣ ድምፅ፣ ንክኪ ወዘተ) ጋር የተያያዙ ችግሮች
- ተደጋጋሚ ባህሪያት
- ውስን ፍላጎቶች
ግምገማው የሰውየውን የልጅነት ዕድገት ታሪክ ለማወቅ ከወላጆች፣ ከአሳዳጊዎች ወይም ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር የሚደረግ ውይይትንም ሊያካትት ይችላል፤ ይህም ትክክለኛ የምርመራ ውጤት ለማግኘት ይረዳል።
በአዋቂነት ዕድሜ ትክክለኛ የASD ምርመራ ውጤት ማግኘት ሰውየው ያለፉትን ተግዳሮቶቹን እንዲረዳ፣ የራሱን ጥንካሬዎች እንዲለይና ትክክለኛውን እርዳታ እንዲያገኝ ይረዳዋል። ወደ አዋቂነት በመሸጋገር ላይ ያሉ ኦቲዝም ያለባቸው ወጣቶችና አዋቂዎች የዕለት ተግባራቸውን እንዲያሻሽሉና በማኅበረሰቡ ውስጥ በተሻለ እንዲሳተፉ የሚረዱ አገልግሎቶችንና ድጋፎችን ለመለየት ጥናቶች እየተካሄዱ ነው።
ሕክምናና ድጋፍ
የASD ሕክምና ምርመራው ከታወቀ በኋላ በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት። ተገቢ እንክብካቤና አገልግሎቶች የሰዎችን ችግሮች በመቀነስ ጥንካሬያቸውን እንዲያጎለብቱና አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲማሩ ስለሚረዱ ቶሎ መጀመር አስፈላጊ ነው።
ASD ያለባቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በጣም የተለያዩ ናቸው፤ ስለዚህ ለሁሉም የሚሆን አንድ ምርጥ የASD ሕክምና የለም። ትክክለኛውን የሕክምናና የአገልግሎቶች ጥምረት ለማግኘት ከጤና ባለሙያ ጋር በቅርበት መሥራት አስፈላጊ ነው።
መድሃኒት
ሐኪም የተወሰኑ ምልክቶችን ለማከም መድኃኒት ሊያዝ ይችላል። በመድኃኒት እርዳታ ASD ያለበት ሰው የሚከተሉት ችግሮች ሊቀንሱለት ይችላሉ፦
- ቁጡነት (በቀላሉ መበሳጨት)
- ጠበኝነት
- ተደጋጋሚ ባህሪ
- ከፍተኛ እንቅስቃሴ
- የትኩረት ችግሮች
- ጭንቀትና ድባቴ
ስለ አዳዲስ የመድኃኒት ማስጠንቀቂያዎች፣ ለታካሚዎች ስለሚሰጡ የመድኃኒት መመሪያዎችና በቅርቡ ስለጸደቁ መድኃኒቶች በምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ድህረ ገጽ ላይ ያንብቡ።
የባህሪ፣ የሥነ ልቦናና የትምህርት ድጋፍ ፕሮግራሞች
ASD ያለባቸው ሰዎች የባህሪ፣ የሥነ ልቦና፣ የትምህርት ወይም የክህሎት ማዳበሪያ ፕሮግራሞችን በሚሰጥ ባለሙያ ዘንድ ሊላኩ ይችላሉ። እነዚህ ፕሮግራሞች ብዙ ጊዜ በጥብቅ የተደራጁና የተጠናከሩ ናቸው፤ ወላጆችን፣ አሳዳጊዎችን፣ ወንድሞችንና እህቶችን እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን ሊያሳትፉ ይችላሉ። እነዚህ ፕሮግራሞች ASD ያለባቸውን ሰዎች በሚከተሉት ሊረዷቸው ይችላሉ፦
- ከሰዎች ጋር የመገናኘት፣ የመግባባትና የቋንቋ ክህሎቶችን መማር
- የዕለት ተግባርን የሚያስተጓጉሉ ባህሪያትን መቀነስ
- ጥንካሬዎችን ማሳደግና በእነሱ ላይ መገንባት
- ራስን ችሎ ለመኖር የሚያስፈልጉ የሕይወት ክህሎቶችን መማር
ሌሎች የእርዳታ ምንጮች
ASD ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ብዙ አገልግሎቶች፣ ፕሮግራሞችና ሌሎች የእርዳታ ምንጮች አሉ። እነዚህን ተጨማሪ አገልግሎቶች ለማግኘት የሚረዱ ጥቂት ምክሮች እነሆ፦
- ስለ ልዩ ፕሮግራሞች ወይም በአካባቢዎ ስላሉ አገልግሎቶች ለማወቅ ሐኪምዎን፣ የአካባቢዎን የጤና ቢሮ፣ ትምህርት ቤትን ወይም የኦቲዝም ተሟጋች ድርጅትን ያነጋግሩ።
- የኦቲዝም የድጋፍ ቡድን ይፈልጉ። መረጃንና ተሞክሮን መለዋወጥ ASD ያለባቸው ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ስለ ሕክምና አማራጮችና ከASD ጋር ስለተያያዙ ፕሮግራሞች እንዲያውቁ ይረዳል።
- ከጤና ባለሙያዎችና ከመምህራን ጋር የሚያደርጓቸውን ውይይቶችና ስብሰባዎች መዝግበው ይያዙ። የትኞቹ ፕሮግራሞችና አገልግሎቶች ተገቢ እንደሆኑ የሚወስኑበት ጊዜ ሲደርስ ይህ መረጃ ሊረዳዎ ይችላል።
- የሕክምና ሪፖርቶችንና የግምገማ ውጤቶችን ቅጂ ያስቀምጡ። ይህ መረጃ ASD ያለባቸው ሰዎች ለልዩ ፕሮግራሞች ብቁ መሆናቸውን ለማሳየት ሊረዳ ይችላል።
ተጨማሪ መረጃ
ነፃ ብሮሹሮችና ሊጋሩ የሚችሉ መረጃዎች
- የኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር፦ ይህ ብሮሹር ስለ ASD ምልክቶች፣ ምርመራና ሕክምና መረጃ ይሰጣል።
- ስለ ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር ሊጋሩ የሚችሉ ዲጂታል መረጃዎች፦ በማኅበረሰብዎ ውስጥ ስለ ASD ግንዛቤና ትምህርት እንዲስፋፋ ያግዙ። ስለ ASD መልዕክቱን ለማዳረስ ምስሎችንና መልዕክቶችን ጨምሮ እነዚህን ዲጂታል መረጃዎች ይጠቀሙ።