የአእምሮ ጤናን የሚነኩ አምስት ዋና ዋና ነገሮች
ስሜትዎና የአእምሮ ጤናዎ ልክ እንደ አካል ጤናዎ ከውስጥም ከውጭም በሚመጡ ነገሮች ይቀረጻሉ። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል።
-
1. የዘር ውርስና የአንጎል ኬሚካሎች
የእያንዳንዱ ሰው አንጎል የተለያየ ነው። አንዳንድ ሰዎች ለውጥረት ወይም ለጭንቀት በቀላሉ እንዲጋለጡ የሚያደርግ የዘር ውርስ (ጂን) ይወርሳሉ፤ የአንጎል ኬሚካሎች ሚዛንም ከሰው ሰው ይለያያል። ሆኖም የዘር ውርስ ሁሉንም ነገር አይወስንም። ሰውነት በአካል እንቅስቃሴ እንደሚጠነክር ሁሉ የአእምሮ ጥንካሬም በልምምድ ይገነባል።
-
2. የሕይወት ገጠመኞች
በሕይወታችን፣ በተለይም በልጅነታችን፣ የሚደርሱብን ነገሮች ዘላቂ ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል። ጉልበተኝነት (ማስፈራራትና ማንገላታት)፣ የቅርብ ሰው ሞት ወይም ሌላ ከባድ ገጠመኝ ስሜትዎን ለረጅም ጊዜ ሊነካ ይችላል። እነዚህ ገጠመኞች የሕይወትዎን አቅጣጫ የግድ አይወስኑም። በድጋፍ ሰዎች ከእነዚህ ገጠመኞች ያገግማሉ።
-
3. የቤተሰብ ታሪክ
የአእምሮ ጤና ችግሮች በቤተሰብ ውስጥ ሊደጋገሙ ይችላሉ። የቅርብ ቤተሰብዎ አባል እንዲህ ያለ ችግር ካለበት የእርስዎም ዕድል ከፍ ሊል ይችላል። ዕድሉ ከፍ ማለቱ ግን ችግሩ የግድ ይደርስብዎታል ማለት አይደለም፤ በቤተሰብ ውስጥ የልብ ሕመም መኖሩም እርስዎን በእርግጠኝነት ይይዝዎታል ማለት አይደለም። የአእምሮ ጤናዎን መንከባከብ አሁንም ለውጥ ያመጣል።
-
4. የዕለት ተዕለት ልማዶች
ምግብ፣ የአካል እንቅስቃሴ፣ እንቅልፍና በስልክ ወይም በቴሌቪዥን ስክሪን የሚያሳልፉት ጊዜ ስሜትንና ጉልበትን ይነካሉ። ጤናማ ምግብ መመገብ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ አዘውትሮ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግና የስክሪን ጊዜን መቀነስ አእምሮዎ በተሻለ ሁኔታ እንዲሠራ ይረዳሉ።
-
5. አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፆችና መድኃኒቶች
አልኮል፣ አደንዛዥ ዕፆችና አንዳንድ መድኃኒቶች በአንጎል ውስጥ ያለውን የኬሚካሎች ሚዛን በመለወጥ ስሜትዎን ሊያወርዱ ወይም ሊያስጨንቁዎ ይችላሉ። ለጊዜው እፎይታ የሚሰጡ ሊመስሉ ይችላሉ፤ በረጅም ጊዜ ግን ችግሩን ሊያባብሱት ይችላሉ። ውጥረትንና አስቸጋሪ ስሜቶችን ለመቋቋም ጤናማ የሆኑ መንገዶች አሉ።
ስሜትዎን የሚነኩትን ነገሮች ማወቅ ምን መለወጥ እንዳለብዎ ለመወሰን ይረዳዎታል። የሚያደርጓቸው ምርጫዎችና የሚያገኙት ድጋፍ ሁለቱም የአእምሮ ጤናዎን ይነካሉ። እርዳታ ካስፈለገዎ ለሚያምኑት ሰው ወይም ለጤና ባለሙያ ይንገሩ።