ድባቴን ለመቋቋም ራስን መንከባከብ፦ ትናንሽ የዕለት ተዕለት እርምጃዎች
ድባቴ በነገሮች የመደሰት ስሜትን ሊያሳጣና ቀላል ሥራዎችን እንኳ ከባድ ሊያደርግ ይችላል። ትናንሽና መደበኛ የራስ እንክብካቤ ልማዶች ሊረዱ ይችላሉ። ሊሞክሯቸው የሚችሉ ስድስት ልማዶች እነሆ፦
-
1. ሰውነትዎን ያንቀሳቅሱ
የአካል እንቅስቃሴ ስሜትን ይረዳል። ፈጠን ብለው በእግር ይራመዱ፣ ይደንሱ ወይም ቀለል ያለ የዮጋ እንቅስቃሴ ያድርጉ። የልብ ምትን የሚያፋጥን እንቅስቃሴ ኢንዶርፊን የተባሉትን፣ ስሜትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የአንጎል ኬሚካሎች እንዲለቀቁ ያደርጋል።
-
2. ከሰዎች ጋር ይገናኙ
ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት ለአእምሮ ጤና አስፈላጊ ነው። ለጓደኛዎ ወይም ለዘመድዎ ይደውሉ ወይም ይጠይቁ፤ ወይም በኢንተርኔት የሚገናኝ የድጋፍ ቡድን ይቀላቀሉ። ስሜትዎን ማካፈልና ሌሎችን ማዳመጥ ሊረዳ ይችላል፤ ይህ ነገር በሌሎችም ላይ እንደሚደርስ ያሳይዎታል።
-
3. በመደበኛ ሰዓት ይተኙ
በየሌሊቱ ከ7 እስከ 8 ሰዓት ለመተኛት ይሞክሩ። በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት ይተኙ፣ ይነሡ፤ ከመተኛትዎ በፊትም የሚያረጋጋ ልማድ ይኑርዎት።
-
4. መደበኛና ገንቢ ምግብ ይመገቡ
የሚበሉት ምግብ በስሜትዎ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ያልተፈተገ እህልና ስብ የሌለው ፕሮቲን ይምረጡ። ስኳር የበዛባቸውንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ይቀንሱ፤ እነዚህ ሊያደክሙዎትና ጉልበትዎን ሊያሳጡ ይችላሉ።
-
5. ስለ ስሜትዎ ይናገሩ
ስሜትዎን በውስጥዎ አምቀው ላለመያዝ ይሞክሩ። ለሚያምኑት ጓደኛ ወይም ዘመድ ያጫውቱ፤ ወይም ቴራፒስት ያግኙ። ስለ ስሜትዎ መናገር እፎይታና ድጋፍ ሊያስገኝልዎ ይችላል።
-
6. የማረጋጊያ ዘዴዎችን ይለማመዱ
ተመስጦ (meditation)፣ የመዝናናት ዘዴዎችና አሁን ላይ ማተኮር (mindfulness) አእምሮን ሊያረጋጉ ይችላሉ። ጥልቅ የአተነፋፈስ ልምምድ፣ በመመሪያ የሚደረግ ተመስጦና ከቤት ውጭ ጊዜ ማሳለፍ ራስን አብዝቶ መንቀፍን ለመቀነስ ይረዳሉ።
ራስን መንከባከብ ገላን መታጠብ ወይም የፊት ቅባት መቀባትን የመሰሉ ደስ የሚሉ ነገሮች ብቻ አይደለም። አእምሮንና ሰውነትን ለመንከባከብ በየጊዜው የሚወሰዱ ትናንሽ እርምጃዎች ናቸው፤ ለምሳሌ ጤናማ ምግብ፣ ለጓደኛ የሚደረግ የስልክ ጥሪ ወይም ለጥቂት ደቂቃዎች በዝግታ መተንፈስ። በተደጋጋሚ የሚደረጉ ትናንሽ እርምጃዎች ውጤታቸው ይጠራቀማል።