ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የአእምሮ ጤና ችግር ምልክቶች
የሁሉም ሰው ስሜት ከፍና ዝቅ ይላል። እነዚህ ለውጦች የዕለት ኑሮዎን ማወክ ሲጀምሩ ግን ትኩረት ይስጧቸው፤ የአእምሮ ጤና ችግር ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
እነዚህ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች እርዳታ የሚያገኙበት ጊዜ መድረሱን ያመለክታሉ፦
የስሜት ለውጦች፦
- የማይለቅ የስሜት መውረድ፦ የማይለቅ ሐዘን፣ ተስፋ መቁረጥ ወይም ቀድሞ ይወዷቸው በነበሩ ነገሮች ላይ ፍላጎት ማጣት አስፈላጊ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ናቸው።
- መቆጣጠር የሚያቅት ቁጣ ወይም ቁጡነት፦ ሁልጊዜ ውጥረት ውስጥ እንዳሉ ከተሰማዎ ወይም በቀላሉ የሚበሳጩ ከሆነ የውጥረት ወይም የጭንቀት ምልክት ሊሆን ይችላል።
- ከፍተኛ የስሜት መፈራረቅ፦ ስሜትዎ በፍጥነት ከከፍተኛ ደስታ ወደ ጥልቅ ሐዘን የሚቀያየር ከሆነ የአእምሮ ጤናዎን ያስመርምሩ።
በዕለት ተግባርና በልማዶች ላይ የሚታዩ ለውጦች፦
- ከልክ በላይ መተኛት ወይም እንቅልፍ ማጣት፦ በእንቅልፍዎ ላይ የሚታይ ትልቅ ለውጥ፣ ለምሳሌ ረጅም የቀን እንቅልፍ ወይም እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች፣ ሌላ ችግር እንዳለ ሊያመለክት ይችላል።
- ከልክ በላይ መመገብ ወይም የምግብ ፍላጎት ማጣት፦ በአመጋገብዎ ላይ የሚታይ ትልቅ ለውጥ፣ ከመጠን በላይ መብላትም ሆነ ምግብ መዝለል፣ እንዲሁ ሌላ ችግር እንዳለ ሊያመለክት ይችላል።
- ከሰዎች መራቅ፦ ቀድሞ ከሚወዷቸው ሰዎችና እንቅስቃሴዎች ራስዎን እያገለሉ ከሆነ የድባቴ ወይም የጭንቀት ምልክት ሊሆን ይችላል።
በአካልና በስሜት ላይ የሚታዩ ምልክቶች፦
- ምክንያቱ ያልታወቀ ሕመምና ቁርጥማት፦ ሁልጊዜ የድካም ስሜት፣ ተደጋጋሚ ራስ ምታት ወይም ምክንያቱ ያልታወቀ ሌላ የሰውነት ምቾት ማጣት አንዳንድ ጊዜ ከአእምሮ ጤና ችግር ጋር ሊያያዝ ይችላል።
- የስሜት መደንዘዝ፦ ምንም ነገር ሳይሰማዎ እንዲሁ ቀኑን እየገፉ ከሆነ አንድ ነገር ልክ እንዳልሆነ ሊያመለክት ይችላል።
- ራስን ወይም ሌሎችን የመጉዳት ሐሳብ፦ ራስዎን ወይም ሌላ ሰውን የመጉዳት ሐሳብ ካለዎት ወዲያውኑ እርዳታ ያግኙ፤ የሚደውሉበትን ቁጥር በአስቸኳይ እርዳታ ገጻችን ላይ ያገኛሉ። ሌሎች ሰዎች በዚህ ጊዜ ሊረዱዎ ይችላሉ።
የዕለት ተግባርን ለመፈጸም መቸገር፦
- ትኩረት ማድረግ ወይም ነገሮችን ማስታወስ መቸገር፦ የመርሳት ወይም ሐሳብን መሰብሰብ የመቸገር ስሜት የውጥረት ወይም የጭንቀት ምልክት ሊሆን ይችላል።
- የዕለት ተግባራትን መወጣት መቸገር፦ ሥራ፣ ትምህርት ወይም ራስን መንከባከብ ከከበደዎ እርዳታ የሚያገኙበት ጊዜ ደርሷል።
እነዚህ አጠቃላይ ምልክቶች ናቸው፤ ሁሉም ሰው ሁሉንም አያጋጥመውም። ስለ አእምሮ ጤናዎ የሚያሳስብዎ ከሆነ እንደ ጓደኛ፣ የቤተሰብ አባል ወይም የጤና ባለሙያ ካሉ ከሚያምኑት ሰው ጋር ይነጋገሩ። እርዳታ መጠየቅ አያሳፍርም።
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት አገልግሎቶችም ድጋፍ ይሰጣሉ።
ሊረዱዎ የሚችሉ አገልግሎቶች (በአሜሪካ)፦
- ብሔራዊ የአእምሮ ሕመም ጥምረት (NAMI)፦ 1-800-950-NAMI (6264)
- ራስን የማጥፋት መከላከያና የቀውስ መስመር (988 Lifeline)፦ 988
- የቀውስ የጽሑፍ መስመር (Crisis Text Line)፦ HOME ብለው ወደ 741741 የጽሑፍ መልእክት ይላኩ
- ጄድ ፋውንዴሽን (The Jed Foundation)፦ jedfoundation.org
- ትሬቨር ፕሮጀክት (The Trevor Project)፦ thetrevorproject.org