ፀረ-ድባቴ መድሐኒቶች ድባቴን ለማከም የሚያገለግሉ መድኃኒቶች ናቸው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሐኪሞች ጭንቀት፣ ህመም፣ እንቅልፍ ማጣት እና መሰል የጤና ችግሮችን ለማከም ፀረ-ድባቴ መድሐኒቶችን ያዝዛሉ።
SSRIs፣ SNRIs እና NDRIs የተለመዱ የጸረ-ድባቴ መድሐኒት ዓይነቶች ናቸው።
እነዚህ መድሃኒቶች ብዙ ጊዜ የሚታዘዙበት ምክንያት ብዙ የድብርት እና የጭንቀት መታወክ በሽታዎች ላይ የሚታዩ ምልክቶችን ስለሚያሻሽሉ እና ከድሮዎቹ የፀረ-ድባቴ መድኃኒቶች ያነሰ የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሏቸው። እንደ ትራይሳይክሊክስ እና ሞኖአሚን ኦክሳይዳይዝ ኢንቢይተሮች (MAOI) ያሉ የድሮ ፀረ-ድባቴ መድሐኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶቻቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ለአንዳንድ ሰዎች ምርጥ አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
ፀረ-ድባቴ መድሐኒቶች ታካሚው ላይ ለመስራት ጊዜ ይወስዳሉ፤ ብዙውን ጊዜ ከ 4 እስከ 8 ሳምንታት። ሆኖም እንቅልፍ ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ድካም፣ የትኩረት ችግር እና የመሳሰሉ ምልክቶች፥ መድሐኒቱ ታካሚውን ከድባቴ ስሜት ከማውጣቱ በፊት፣ ቀደም ብለው ሊሻሻሉ ይችላሉ። ታካሚዎች መድሐኒቱ እነሱ ላይ መስራት አለመስራቱን ከመወሰናቸው በፊት የሀኪማቸውን መመሪያዎች መከተል እና መድሃኒቱን እስከታዘዙት ጊዜ ድረስ መውሰድ አለባቸው።
የ SSRIs እና የሌሎች ፀረ-ድባቴ መድኃኒቶች ሊያስከትሉ የሙችሏቸው የተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች የሆድ ቁርጠት፣ ራስ ምታት እና ከወሲብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው። የጎንዮሽ ጉዳቶቹ በአጠቃላይ ቀላል እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ የሚሄዱና የሚጠፉ ናቸው። የጎንዮሽ ጉዳቶች በቀላሉ የሚታይባቸው ሰዎች መድሐኒቱን በትንሽ መጠን በመጀመር፣ በየቀኑ በትንሽ ትንሹ መጠኑን እየጨመሩ በመሄድ እና መድሃኒቱን የሚወስዱበትን ጊዜ (ለምሳሌ በመኝታ ሰዓት ወይም በምግብ) ከሁኔታቸው ጋር በማጣጣም የጉዳቱን መጠን መቀነስ ይችላሉ።
Esketamine የተሰኘ የጸረ-ድባቴ መድሐኒት ታካሚው ቢያንስ ሁለት የፀረ-ድባቴ ቴራፒዎችን ከሞከረ በኋላ መሻሻል ካላሳየ የሚታዘዝ አዲስ ከFDA ፍቃድ ያገኘ ለሕክምና ቶሎ ለማይታዘዝ የድባቴ በሽታ ከሚታዘዙ መድኃቶች ጎራ የሚመደብ መድሐኒት ነው።Esketamine በአፍንጫ የሚረጭ በጤና ጣብያ፣ በክሊኒክ ወይም ሆስፒታል ውስጥ የሚገኝ መድሐኒት ነው። በፍጥነት፣ ሁለት ሰዓታት ውስጥ፣ የሚሰራ የድባቴ ማስታገሻ መድሐኒት ነው። የደባቴ ምልክቶች እየተሻሻሉ እንዲቀጥሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚዋጡ የፀረ-ድባቴ መድሐኒቶችን መውሰዳቸውን ይቀጥላሉ።
እንደ “ትሪፕታን መድኃኒቶች (ብዙውን ጊዜ ማይግሬን ራስ ምታትን ለማከም ጥቅም ላይ ይውላሉ) እና ሴንት ጆን ዎርት (የአመጋገብ ማሟያ) ያሉ በሴሮቶኒን ሲስተም ላይ ከሚሠሩ መድኃኒቶች ወይም ተጨማሪ መድኃኒቶች ጋር በማጣመር ያልተለመደ ነገር ግን ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ሴሮቶኒን ሲንድሮም ተብሎ የሚጠራ በሽታ ያስከትላል። ሴሮቶኒን ሲንድረም የሚከተሉ ምልክቶች ያካትታል፦ ከፍተኛ የአእምሮ መረበሽ፣ የጡንቻ መንቀጥቀጥ፣ ቅዠት (ሌሎች የማያዩትን ማየት ወይም መስማት)፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር እና ያልተለመዱ የደም ግፊት ለውጦች ናቸው። አብዛኛው ሰው እንደዚህ አይነት ከባድ ምላሾች አያጋጥማቸውም። ሐኪሞች ከአንድ በላይ መድሒኒቶችን በማዋኸድ የተዘጋጁ፣ ከተለመደው ከፍ ያለ ሪስክ ያለባቸውን፣ መድሃኒቶች ሲያዝዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ክትትል ማድረግ አለባቸው።
የሚከተለው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፦ ከ 25 ዓመት በታች የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ፀረ-ድባቴ መድሐኒታችን ሲወስዱ፣ በተለይም መድሃኒቱን የጀምሩ አከባቢ ወይም ዶዙ ሲቀየር፣ ራስን የማጥፋት ሀሳቦች የማሰብ እድላቸው ከፍ ሊል ይችላል። ፀረ-ድባቴ መድሐኒት የሚወስዱ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚከኙ ሰዎች፣ በተለይም በመጀመሪያዎቹ የሕክምና ሳምንታት፣ የተለየ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል።
This post is also available in:
English (እንግሊዝኛ)
